ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ለምርምር ግብዓትና ለተለያዩ ፋይዳ ያላቸው ልዩ ልዩ ቅርሶችና ሥጦታዎችን ተረከበ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ለምርምር ግብዓትና ለተለያዩ ፋይዳ ያላቸው ልዩ ልዩ ቅርሶችና ሥጦታዎችን ተረከበ። 

ተቋሙ የተረከባቸው ከተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ግለሰቦች ሲሆን ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ለታሪክ ምርምርና ለዕይታ የሚውሉ ታሪካዊ ቁሳቁሶች ናቸው ተብሏል።  

ከእነዚህም መካከል የመካከለኛው ዘመን መገበያያ ሳንቲሞች፤ የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ፎቶዎችና ዶክመንቶች እንዲሁም ሌሎች መጻሕፍትና ቁሳቁሶችን ተረክቧል።


 

ከሥጦታዎች መካከልም በ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ዓመታት በኖሩ ጀርመናዊያን ፎቶ አንሺዎች የተነሱና የዘመኑን ሁለንተናዊ መልኮች የሚገልፁ ምስሎችን ያካተቱ ሦስት የፎቶ አልበሞች እንዲሁም በጀርመናዊ ፕሮፌሰር ኒል ሙኑሮ የተበረከቱ የ1973 የተቀረጸ ፊልም ይገኙበታል።

እንዲሁም በዶክተር ሁሴን ሰይድና በአቶ ወንድማገኘሁ ግዛው የተሰባሰቡ 22 የመካከለኛው ዘመን መሐልቆች/ሳንቲሞች፣ የዕውቁ ጋዜጠኛ ጌታቸው ተድላ 65 ፎቶግራፎች፣ የአፄ ኃይለሥላሴ ፓስፖርትና ሰነዶች እንዲሁም ከ300 በላይ መፃሕፍት ይገኙበታል።


 

የርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ታከለ መርዕድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን በተገኙበት በራስ መኮንን አዳራሽ ተካሂዷል።

ተቋሙም ሥጦታዎችን ላበረከቱ ግለሰቦች ዕውቅና ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም