ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋፋት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤መጋቢት 6/2016(ኢዜአ)፦የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋፋት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለፀ።

ከ 3 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ  ዜጎችን በግለሰብ ደረጃ ተጠቃሚ የሚያደርግ ኮምፖነንት 3 ነጥብ 2 የተሰኘ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፕሮጀክት ማስጀመሪያና የባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።  

በማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የዓለም ባንክ፣ የባንክና ፋይናንስ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 

የውኃና ኢነርጂ ሚንስትር አማካሪ ጎሳዬ መንግሥቴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን መርኃ ግብር እየተተገበረ ነው።

ከዓለም ባንክ በተገኘ 500 ሚሊየን ዶላር  ያልተማከለ የኤሌክትሪክ ኃይልና መብራት ለኢትዮጵያ የተሰኘ ፕሮጀክት እ.አ.አ ከ2021 ጀምሮ እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል።

ፕሮጀክቱ በመላው አገሪቱ በቤተሰብ፣ በማኅበራዊና በንግድ ተቋማት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በዋናነት የገጠር ማኅበረሰቡን የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ማስፋት እንደሆነ ተናግረዋል።

ለአብነትም 240 ሺህ ለሚደርሱ የገጠር አካባቢ ማኅበረሰቦችና ተቋማት የሶላር ሚኒ ግሪድ አስተማማኝ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

1ሺህ 400 የገጠር ትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማትን የሶላር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም እንዲሁ።

በዛሬው ዕለት የተጀመረው 750 ሺህ ቤተሰብ የሶላር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚያደርገው የኮምፖነንት 3 ነጥብ 2 ም መርኃ ግብርም የዚሁ ፕሮጀክት አካል መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ዋቄ በበኩላቸው መርኃ ግብሩ በ42 ሚሊየን ዶላር በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ቅንጅት የሚተገበር ነው ብለዋል።  


 

መርኃ ግብሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ባልሆነባቸው አካባቢዎች የኃይል ተደራሽነት እንዲሁም የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል። 

ባንኩ የሶላር ቴክኖሎጂ አስመጪና አቅራቢዎች የፋይናንስ አቅርቦት በማድረግ ኅብረተሰቡ የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽዖ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም