ቀጥታ፡

የጎረቤት አገራት ለሚጠይቁት ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል - ኢንጂነር ኃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2016(ኢዜአ)፡- የጎረቤት አገራት ለሚጠይቁት ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ኃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ። 

ሚኒስትሩ ኢንጂነር ኃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ጸጋ ተጠቅማ በምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይልና በመስኩ ያላት የአስተዳደር ብቃት ተከትሎ አገራት የኃይል ግዥ ለመፈጸም ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው።

በዚህም ጅቡቲና ሱዳን እንዲሁም ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር በኃይል መተሳሰራቸውን ገልጸዋል።

ከኬንያ ጋር የተደረገው የኃይል ትስስር ታንዛኒያን እንዲሁም ደቡብ አፍሪካን ጭምር የሚያስተሳስር መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኤሌክትሪክ ኃይል በማስተሳሰር ትልቅ ድርሻ እየተወጣች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ እያቀረበች ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚመነጨው ከውኃ መሆኑና ይህም የአየር ንብረት ብክለት የማያስከትል መሆኑ ተፈላጊነቱ እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።

የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል በዝቅተኛ ታሪፍ መሆኑም ተፈላጊነቱ እንዲጨምር ማስቻሉን ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ የጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በየዓመቱ 15 በመቶ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን ነው ያስረዱት።

በቀጣይም የጎረቤት አገራት ለሚጠይቁት ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም መፈጠሩንም ነው ያመላከቱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም