ቀጥታ፡

በፕሪሚየር ሊጉ ቀዳሚ ስፍራ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና መቻል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት መርሐ ግብር የሁለተኛ ቀን ውሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመቻል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በድሬዳዋ ስታዲየም ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ እየተመራ በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ግስጋሴ እያደረገ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውድድር ዓመቱ እስከ አሁን ባደረጋቸው 17 ጨዋታዎች በ11ዱ ሲያሸንፍ በ3ቱ ተሸንፏል፤ ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።


 

ቡድኑ 31 ግቦችንም ሲያስቆጥር 16 ጎሎች አስተናግዷል፤ በ36 ነጥብ እና በ15 የግብ ክፍያ ሊጉን እየመራ ይገኛል።

ንግድ ባንክ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ ሸንፈት አጋጥሞታል፤ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው መቻል በፕሪሚየር ሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 17 ጨዋታዎች 10ሩን ሲያሸንፍ 4 ጊዜ ተሸንፏል። ሶስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።


 

23 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 18 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ክለቡ በ33 ነጥብና በ5 የግብ ክፍያ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የመቻል አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ክለቡ በ17ኛ ሳምንት መርሐ ግብር  ከባህር ዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ በተጋጣሚ ቡድን አሰልጣኝ ላይ ለጠብ የሚያነሳሳ የስነ-ምግባር ድርጊት ፈጽመዋል በሚል ለአራት ጨዋታ መታገዳቸውን ተከትሎ ቡድናቸውን በሜዳ ተገኝተው አይመሩም።

በተጨማሪም አሰልጣኙ አምስት ሺህ ብር እንዲከፍሉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ  መወሰኑ ይታወቃል።

በሌላኛው የ18ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ከቀኑ 10 ሰዓት ድሬዳዋ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በአሰልጣኝ ኮማንደር ሽመልስ አበበ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሶስቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ወጥቷል።

ክለቡ በ25 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች በሶስቱ ሲያሸንፍ በአንዱ ሽንፈት አጋጥሞታል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመራው ሀዋሳ ከተማ በ22 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ባህር ዳር ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 3 ለ 1፤ አዳማ ከተማ ሀምበሪቾ ዱራሜን 3 ለ 0 አሸንፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም