የነዳጅ ዋጋ እንዲስተካከል መደረጉ የነዳጅ ኮንትሮባንድ እንዲቀንስ አስችሏል - አቶ ገብረመስቀል ጫላ - ኢዜአ አማርኛ
የነዳጅ ዋጋ እንዲስተካከል መደረጉ የነዳጅ ኮንትሮባንድ እንዲቀንስ አስችሏል - አቶ ገብረመስቀል ጫላ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2016 (ኢዜአ)፦ የነዳጅ ዋጋ እንዲስተካከል መደረጉ የነዳጅ ኮንትሮባንድ እንዲቀንስ ማድረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ተናገሩ።
የኢትዮጵያን የንግድ ሥርዓት ለማዘመን የተከናወኑ ዐበይት ተግባራትን አስመልክቶ ሚኒስትሩ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኮንትሮባንድ የገቢና የወጪ ንግድ ሥርዓትን በማቀጨጭ የአገሪቱ ቁልፍ ችግር መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ህገ-ወጥ ነጋዴዎች በቁም እንስሳት፣ በጫት፣ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች የሚያካሄዱት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በወጪ ንግድ ሥርዓቱ ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል።
በኮንትሮባንድ የተሰማሩ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሀገርንና ህዝብን የሚጎዱ ድርጊቶችን እየፈጸሙ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮንትሮባንድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቁልፍ ችግር ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል።
የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠርም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የጸጥታና ጉምሩክ ተቋማት ግብረ ሃይል ተደራጅቶ እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ከጎረቤት አገራት ጋር ሲነፃጸር ዝቅተኛ በመሆኑ ሙሉ ቦቴ ጭምር ወደ ጎረቤት አገራት ሄዶ የሚሸጥበትና ኢትዮጵያም ስትፈተንበት የቆየችው ጉዳይ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም ቀስበቀስ በተካሄደው የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያ ከጎረቤት አገራት ተመሳሳይ እንዲሆን በማድረግ ኮንትሮባንድ እንዲቀንስ ማድረጉን ገልጸዋል።
አሁንም የተወሰነ የነዳጅ ኮንትሮባንድ ዝንባሌ ቢስተዋልም በተወሰደው የማሻሻያ እርምጃ ከሀገር የሚወጣበት ሥርዓት እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም የነዳጅ አቅርቦትን በዘመናዊ መልኩ ለማስተዳደር ከመነሻው እስከ ስርጭት ሂደቱ በኦንላይን ሥርዓት ለመከታተል ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የውጭ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት የሚሳተፉበትን ምኅዳር ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።