በከፍታ የታጀበ ስኬት

1973

ለህጻናትና ታዳጊዎች መልካም ስብእና የሚያግዙ ጽሁፎችን ያዘጋጀችው ኤሪን ሶዴርበርግ ዶውኒንግ 'JUST KEEP WALKING' በሚለው መጽሃፏ ባደራጀችው ገጸባህሪ አማካይነት “አንተ መልካምና ስኬታማ ሆነህ ሳለ ጥቂት ሰዎች ስለአንተ መጥፎነት አብዝተው መጨነቅና ማውራት ከጀመሩ የምትሄድበት መንገድም ሆነ አካሄድህ ትክክል ነውና መራመድህን አታቁም። ብዙሃኑ የስኬትህ ተካፋይና የስኬትህ አጋር ስለሆኑ የጥቂቶቹን ጫጫታ ከምንም ካለመቁጠር ተራመድ ብዙ አፍራሽ ወሬዎች ያንተን ስኬት የመመስከር አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑን አትዘንጋ። መቆም የሽንፈት ምልክት ነውና” ትለናለች። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላለፉት 78 ዓመታት በከፍታ የዘለቀ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስምና ዝናው የገነነ ተቋም ነው። አየር መንገዱ ታህሳስ 21 ቀን 1938 ዓ.ም ተመስርቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ በረራውን መጋቢት 30 ቀን 1938 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ካይሮ አድርጓል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየዘመኑ በአቪዬሽን ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅና አሰራሮችን በማዘመን ራሱን እያደራጀ የኢትዮጵያ ኩራት ከመሆን አልፎ የአፍሪካ ምልክት ሆኖ ዘልቋል። ዛሬ ላይ የ152 ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ  በምስረታው ወቅት ከአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል የተገዙና በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ያገለገሉ አምስት አውሮፕላኖች ብቻ እንደነበሩት መረጃዎች ያመለክታሉ። 

በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በዓመት ከ22 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን እንደሚያስተናግድ የሚነገርለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞችን ፍላጎትና ምቾት ለመጠበቅ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ጨምሮ 31 አውሮፕላኖች ለመግዛት ከአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል።  እነዚህን ተጨማሪ አዳዲስ አውሮፕላኖችን ቁጥር ጨምሮ የሚገነባቸው ዘመናዊ አየር መንገዶች ሲደመሩ በአፍሪካ ግዙፍ ተቋምነቱን ይበልጥ የሚያረጋግጥ ያደርገዋል። 

የበረራ አድማሱን በየጊዜው እያሰፋ የሚገኘው አየር መንገዱ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ 134 መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን በሀገር ውስጥ ወደ 22 መዳረሻዎች ይበራል። ከዚህ ውስጥ 60 የበረራ መዳረሻዎቹ አፍሪካ ውስጥ ነው።

አየር መንገዱ ከ55 ሚሊየን ዶላር በላይ አስገንብቶ ወደ ስራ ያስገባው ዘመናዊ የካርጎ ማእከል ከምስራቅ አፍሪካ ብሎም ከአፍሪካ ከፍተኛ ተብሎ ተመዝግቦለታል። በ15 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ግንባታው ያረፈው የካርጎ ማዕከል ለኤሌክትሮኒክስ ግብይት (ኢ ኮሜርስ) አገልግሎት የሚውል ሲሆን የካርጎ አገልግሎት እየሰፋ መምጣት አየር መንገዱ የሚሰራቸው ተያያዝ በርካታ ተግባራት መስፋት፣እንዲሁም የዲጂታል ግብይት ተመራጭ መሆን ለማእከሉ ግንባታ ምክንያት ተብለው ተጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በማህበራዊ መስክ ከሚታወቅባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ሴቶችን በማብቃትና የጾታ እኩልነትን በማስተግበር ረገድ አርአያነት ያለው ተግባር መፈጸሙ ነው። በየዓመቱ የሚታሰበው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር ማርች 8 በሚከበርበት ዕለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላለፉት በርካታ አመታት ወደ ተለያዩ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ሙሉ ለሙሉ በሴቶች ብቻ የተመራ በረራን በማደረግ ዓለም አቀፍ ዝናን አትርፏል። አየር መንገዱ ዘንድሮ ለ9ኛ ጊዜ "ሴቶችን በማብቃት አፍሪካን ማስተሳሰር" በሚል መሪ ቃል ከአዲስ አበባ ወደ ለንደን በሴቶች ብቻ የተመራ የተሳካ በረራ አድርጓል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመንገደኞች በሚሰጠው ዘመኑን የዋጀና ቀልጣፋ አገልግሎት በየጊዜው የተለያዩ ሽልማቶች ባለቤት መሆን የቻለ ተቋም ነው። ለአብነት የቅርብ ጊዜያቶችን ለማንሳት ያህል ባሳለፍነው ዓመት በአየርላንዷ ደብሊን በተዘጋጀ መርሐ-ግብር ላይ በዓመታዊው የ“አፔክስ” የመንገደኞች ምርጫ “ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ” ሽልማትን አሸንፏል፡፡

በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ የአየር ጭነት ኢንዱስትሪ ጉባኤ "ኤር ካርጎ ኤሮፕ" እ.አ.አ በ2021 ባካሄደው የበይነ መረብ የሽልማት ስነ ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የካርጎና የሎጅስቲክ አገልግሎት የ2021 የአየር ጭነት ኢንዱስትሪ የደንበኞች እንክብካቤ ዘርፍ ሽልማት አግኝቷል። በአውሮፓውያኑ 2024 ዓመታዊውን የብሪክስ አባል ሀገራት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የ2024 ሽልማት ላይ “የኮርፖሬት የዘላቂነት ስኬት ሽልማት” አሸናፊ ሆኗል።

አየር መንገዱ በትላልቅ ስኬቶች የማለፉን ያህል ከባድ ፈተናዎችንም ተጋፍጦ በጽናትና በስኬት አልፏል። መላውን ዓለም ያዳረሰው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አንዱ ማሳያ ነው። በዚያን ጊዜ የመንገደኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ ምክንያት በዓለም ደረጃ በርካታ አየር መንገዶች በረራ በማቋረጥ ችግር ውስጥ ወድቀዋል። 

በዚህ ፈታኝ ወቅት አየር መንገዱ የስትራቴጂ ለውጥ በማድረግ  አንዳንድ የመንገደኞች አውሮፕላኖቹን ወደ ዕቃ ጫኝ በመቀየር ጭምር ትኩረቱን ጭነት ማጓጓዝ ላይ አድርጓል። በዚያን ፈታኝ ወቅት አየር መንገዱ የቀየሰውን ስትራቴጂ በመቃወም ከውስጥም ከውጭም ከተለያዩ አቅጣጫዎች ትችትን አስተናግዷል። 

ይሁን እንጂ አየር መንገዱ ፈተናውን በመቋቋም እንደሌሎቹ ሀገራት አውሮፕላኖች በረራ የማቋረጥ እጣ ሳይገጥመው በታላቅ ብልሃት ማለፍ የቻለ ተቋም መሆኑ ተመስክሮለታል። በዚህም በካርጎ አገልግሎት ገቢ ከማገኘቱም ባሻገር ክትባትን ለዓለም በማዳረስ ወረርሽኙ ለመግታት በተደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት ውስጥ የራሱን አሻራ አኑሯል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የራሱ የአውሮፕላን አብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምሕርት ቤት ሲኖረው የግል አብራሪ እና የንግድ አውሮፕላን አብራሪ ፈቃድ በመስጠት የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ዜጎችን በማሰልጠን ከአራት አስርተ ዓመታ በላይ ልምድ አካብቷል። አየር መንገዱ በሚያስተዳድረው ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ የበረራ ባለሙያዎችን በቅርቡ ያስመረቀ ሲሆን ምሩቃኑ ከታንዛንያ ከደቡብ ሱዳን ከኒጀር ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከቶጎ እና ከማዳጋስካር መሆናቸው ደግሞ የአየር መንገዱን የፓንአፍሪካኒስት መንፈስ አጉልቶ ያሳየ አድርጎታል። 

ስኬቶቹ በዚህ ያላበቁት አየር መንገዱ  የእድገት ግስጋሴውን እንደቀጠለ ይገኛል። ከሰሞኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአድዋ ድል መታሰቢያ በተካሄደ ደማቅ ስነ-ስርዓት ላይ ለአምስት ተቋማት ‘የኢትዮጵያ ተቋማት ስኬት ሽልማትን’ አበርክተዋል። በዚህ ወቅት ከተሸለሙት ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲሆን ሽልማቱ ለወደፊትም ለላቀ ስኬት የሚያዘጋጀው እንደሆነ ይታመናል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም