በኢትዮጵያ የቲቢ በሽታ የማህበረሰብ ስጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተያዘው ግብ እንዲሳካ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የቲቢ በሽታ የማህበረሰብ ስጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተያዘው ግብ እንዲሳካ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የቲቢ በሽታ በ2030 የማህበረሰብ ስጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተያዘው ግብ እንዲሳካ የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ተናገሩ።
በመተንፍሻ አካላት በሽታዎች ላይ የሚሰራው የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ በቲቢ፣ አስም፣ ስር የሰደደ የመተንፍሻ አካል ችግር፣ የሳንባ ካንሰርና ተያያዥ የጤና ጉዳዮች ላይ ያተኮረውን 10ኛ ዓመታዊ ኮንፈረንስ አካሂዷል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በየዓመቱ በቲቢ በሽታ ከ156 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው የሚያዙ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 21 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት እንደሚያልፍ ተናግረዋል።
በቀጣይ 7 ዓመታት መድህኃኒትን የተላመደ ቲቢን ለማጥፋት ግብ ተይዞ ሁሉን አቀፍ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የሳምባ ፣ የጡት እና የማህጸን ካንሰርን ህክምናን ለማስፋት ዘመናዊ የህክምና መሳሪዎች ወደ አገልግሎት መግባታቸውን አንስተዋል።
በጤና ሚኒስቴር የቲቢና የሥጋ ደዌ ፕሮግራም አስተባባሪ ታዬ ለታ በበኩላቸው፥ የቲቢ በሽታ ህክምና አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ በ70 ጤና ተቋማት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የቲቢ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ፕሮግራምን በመተግበሯ የበሽታውን የመከሰት ምጣኔ በ38 በመቶ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በሽታውን ለመከላከል በትራንስፖርት፣ በቤት ውስጥ መስኮት መክፍት እንደሚገባ ጠቁመው የበሽታው ምልክቶች የሆኑት ሳል፣ የድካም ስሜት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ሲከሰት ወደ ጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ራሄል አርጋው፥ ሶሳይቲው የሳንባ፣ የአስም እንዲሁም ስር የሰደዱ የመተንፈሻ አከላት ሕመሞችን በዘለቂነት ለመከላከል በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።