በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ75 ሺህ ለሚልቁ ሴቶች የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ75 ሺህ ለሚልቁ ሴቶች የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል
ሀዋሳ ፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፖርኮች ከ75 ሺህ የሚበልጡ ሴቶች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
"ሴቶችን እናብቃ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተከብሯል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮሮፖሬሽን የስርዓተ ጾታ ማህበራዊ ሃላፊነት መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ልክየለሽ አባይ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የሴቶች ቀን ማክበር ሴቶችን ለማብቃት፣ ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ በትኩረት በመስራት ሊሆን ይገባል ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ በሚገኙ 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ፓርኮቹ በርካታ የስራ እድል በሚፈጥሩ መስኮች እንደተሰማሩ ጠቅሰው፤ "በልማትና በውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው" ብለዋል።
በእስካሁኑ ሂደት የስራ እድል ከተፈጠረላቸው 100 ሺህ ዜጎች መካከል ከ75ሺ የሚበልጡት ወጣት ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በፓርኮቹ በተለያየ የስራ መስክ የተሳተፉ ሴቶች በቆይታቸው የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ራሳቸውን ማብቃትና ከተቀጣሪነት መውጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኦፕሬሽንና ማኔጅመንት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ በልአንተ ጠብቀው በበኩላቸው፤ ፓርኩ በስራ እድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና የውጭ ምንዛሪ መጨመር በሚያስችሉ ተግባራት ላይ በትኩረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ በልአንተ እንዳሉት፤ በፓርኩ 22 የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በፈጠሩት የስራ እድል ከ25 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል፤ ከ85 ከመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
በዚህም ፓርኩ "የሴቶችን አቅም ማጎልበት ላይ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል።
በሲዳማ ክልል የስራ እድል ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የሴቶች ተጠቃሚነት 45 ከመቶ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ክልል ስራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሐገረጽዮን አበበ ናቸው።
የኢንዱስትሪ መስፋፋት በክልሉ ያለውን የስራ እድል ፈላጊ ለማስተናገድ እንደሚያግዝ ጠቅሰው፤ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተለይ ለሴቶች የፈጠረው እድል ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ክልል ሴቶችን በፖለቲካ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እድሎች በመኖራቸው ሴቶች ራሳቸውን በማብቃት በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የሴቶች ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወይዘሪት ነስራ አብዶሽ፤ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮንፌዴሬሽኑ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚሰሩ ሴት ሰራተኞችን በማደራጀት የተለያዩ ሙያ ክህሎት ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ማገዙን ጠቅሰዋል።
በመድረኩ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን የህይወት ልምዳቸውንና ጥናታዊ ጽሁፎችን አቅርበዋል።