በኢንዱስትሪዎች የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የሚያስችል አዲስ እሳቤ ተቀርጾ ወደ ስራ ተገብቷል-የስራና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢንዱስትሪዎች የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የሚያስችል አዲስ እሳቤ ተቀርጾ ወደ ስራ ተገብቷል-የስራና ክህሎት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦ በኢንዱስትሪዎች የአሰሪና ሰራተኛ መካከል ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት በመፍጠር ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የሚያስችል አዲስ እሳቤ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዳንኤል ተሬሳ ገለጹ።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር "አዲስ የኢንዱስትሪ ባህል ለሁለንተናዊ የስራ ብቃት እና ኢኮኖሚ ሽግግር" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪ ማህበረሰብ ምክክር ማስጀመሪያ መርሀ ግብር እና የአመቻቾች እና አስተባባሪዎች ስልጠና በአዳማ ከተማ አስጀምሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዳንኤል ተሬሳ፣ የአዳማ ምክትል ከንቲባ ሙላቱ ዳባ የዘርፉ ተዋንያን እና ሰልጣኞች ተገኝተዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዳንኤል ተሬሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የስልጠናው ተሳታፊዎች ከኢንዱስትሪው ማህበረሰብ ተወክለው የመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዓላማውም በቀጣይ በአሰሪና ሰራተኛ መካከል የሚኖሩ ግንኙነቶችን በማሻሻል አለመግባባቶች ሲኖሩም በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለጋራ ጥቅምና አላማ መልካም ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ነው ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም በአሰሪና ሰራተኛ መካከል ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነትን ከመፍጠር አኳያ የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት አዳዲስ አሰራሮችን ለመተግበር አዲስ እሳቤ ቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን አንስተዋል።
ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ምህዳር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በዘርፉ የሚደረግ የተናጠል እና የጋራ ምክክር ስርዓት መዘርጋት ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል።
በአሰሪና ሰራተኛ መካከል ሰላማዊ የስራ ምህዳር እንዲኖር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰው፤ ሰልጣኞችም የምክክሩን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በስራና ክህሎት የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ተካልኝ አያሌው በስልጠናው ከ80 ድርጅቶች የተውጣጡ 400 ተወካዮች እየተሳተፉ ነው ብለዋል።
ስልጠናው የንግግር ባህልን በማስፋት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኢንዱስትሪ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተጀመረ የሪፎርም ስራ መሆኑን ጠቁመዋል።