ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንት ሣሕለወርቅ ዘውዴ የ11 ሀገራትን አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦  የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣሕለወርቅ ዘውዴ  በኢትዮጵያ የተሾሙ የ11 ሀገራትን  አምባሳደሮች  የሹመት ደብዳቤ  ተቀበሉ።

ፕሬዝዳንቷ የሹመት ደብዳቤያቸውን የተቀበሏቸው ከኤስያ ሦስት ሀገራት፣ ከአፍሪካ አምስት ሀገራት እንዲሁም ከአውሮፓ ሦስት ሀገራት በኢትዮጵያ የተሾሙ አምባሳደሮችን ነው።

የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዝዳንቷ ያቀረቡት የኬንያ፣ የኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ማላዊ፣  ኳታር፣ ጃፓን፣ አዘርባጃን፣ ስፔን፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ እና አርሜንያ ተወካዮች አምባሳደሮች ናቸው።


 

ፕሬዝዳንት ሣሕለወርቅ ከሁሉም አምባሳደሮች ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ ከየሀገራቱ ጋር ያላትን የሁለትዮሸ ግንኙነት ለማጠናከር  ቁርጠኛ መሆኗን አብራርተዋል።


 

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያላትን ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያስከብርና በሚያስቀጥል መልኩ እንደምትሰራም በውይይታቸው አንስተዋል።

አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትብብር እንደሚያደርግም ፕሬዝዳንቷ አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም