ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ሠራዊት በተባበሩት መንግስታት የተሰጠውን ሰላም የማስከበር ተልዕኮን በታላቅ ህዝባዊ ወገንተኝነትና ጀብድ በመፈፀም ላይ ይገኛል

ሁርሶ ፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ሠራዊት በተባበሩት መንግስታት የተሰጠውን ሰላም የማስከበር ተልዕኮን በታላቅ ህዝባዊ ወገንተኝነትና ጀብድ በመፈፀም አኩሪ ታሪክ እያስመዘገበ ይገኛል ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት የጤና መምሪያ ዋና ሃላፊ ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ ይልማ አስታወቁ።

ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ ይልማ ይህን የገለጹት የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለደቡብ ሱዳን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያሰለጠናቸውን የሠራዊት አባላትና አመራሮች ዛሬ አስመርቆ ለግዳጅ ዝግጁ ባደረገበት ወቅት ነው።


 

የተግባርና የንድፈ ሐሳብ ወታደራዊ ስልጠናዎችን የተከታተሉና ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ የሚሰማሩት  እነዚሁ የሰላም አስከባሪ የ18ኛ እና የ19ኛ ሞተራይዝድ ሬጅመንት ሻለቃ አመራሮችና አባላት መሆናቸውም ታውቋል።

በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የጤና መምሪያ ዋና ሃላፊ ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ ይልማ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት በተባበሩት መንግስታት የተሰጠውን ሰላም የማስከበርና ዘላቂ ሰላም የማስፈን ተልዕኮን በታላቅ ህዝባዊ ወገንተኝነትና ጀብድ በመፈፀም አኩሪ ታሪክ እያስመዘገበ ይገኛል።

ዛሬ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተገቢውን ስልጠና አጠናቀው የተዘጋጁ የሠራዊቱ አባላትና አመራሮች ኢትዮጵያ በጎረቤት አገራት  ሰላም ለማስከበር የተሰጣትን  ኃላፊነትና ተልዕኮ በታላቅ ቁርጠኝነት  በመወጣት ያላትን ዝናና ከፍታ ማስቀጠል እንዳለባቸው አስታውቀዋል።

ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ አክለውም ወደ ደቡብ ሱዳን የሚጓዙት የሰላም አስከባሪ የሠራዊት አባላትና አመራሮች የኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት የጀመረውን የፕሮፌሽናሊዝም የሠራዊት ግንባታ ሂደት በተግባር የሚያዳብሩበት አጋጣሚ ይፈጥራል። 

በመከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አዳምነው መንግስቴ በበኩላቸው ሠራዊቱ መልካም እሴቶችን በመላበስ ማንኛውንም ግዳጅ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ "በታላቅ ጀግንነትና ህዝባዊ ወገንተኝነት የመፈፀም ብቃቱ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ተመራጭ የሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሆን አድርጎታል" ብለዋል።


 

ይህንኑ ገድል ለማስቀጠልና የተጣለባቸውን የአምባሳደርነት ሚና ለመወጣት  የቀሰሙት የፕሮፌሽናሊዝም የውትድርና ሙያና ጥበብ እንደሚያግዛቸው ጠቅሰው፤ ተልዕኮውን ስኬታማ ለማድረግ በጥንቃቄ መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የሰላም አስከባሪ የ18ኛ እና የ19ኛ ሬጅመንት ሻለቃዎች አባላትና አመራሮች የተጣለባቸውን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በአስተማማኝ መንገድ መወጣት የሚያስችላቸው የተግባር፣ የንድፍና የሥነ ልቡና መሠረታዊ ዕውቀትና ጥበቦች መቅሰማቸውን የገለፁት ደግሞ የሁርሶ ኮንቲንጀንት ትምህርት ቤት አዛዥ  ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ ናቸው።


 

ለሰላም ማስከበር ግዳጅ ዝግጁ የሆኑት የሠራዊት አባላትና አመራሮች የተጣለባቸውን ተልዕኮ በስኬት እንዲወጡም በማስገንዘብ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም