የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ጥበቃ ማኅበራት ጥምረት ተቋቋመ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ጥበቃ ማኅበራት ጥምረት ተቋቋመ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦ የሸማቾችን መብትና ጥቅም በተደራጀ መልኩ ለማስጠበቅ የሚሰራ የኢትዮጵያ ሸማቾች ጥበቃ ማኅበራት ጥምረት መቋቋሙን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
የፊታችን ሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሸማቾች ቀን የተመለከተ የባለድርሻ አካላት የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በኢትዮጵያ ለ11ኛ ጊዜ፣ በዓለም ደግሞ ለ41ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም አቀፍ የሸማቾች ቀን “በኅብር መብታችንን እናስከብር” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል ተብሏል።
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሀገር ውስጥ ንግድና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ መስከረም ባሕሩ፤ በንግድ ስርዓት ውስጥ የሸማች አደረጃጀቶች ቁልፍ ሚና ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የሸማቾችን መብት በማስከበር ረገድ በክልሎችም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የሸማች ማኅበራት ሚና ከፍተኛ እንደነበር አንስተዋል።
በክልሎች የተደራጁ የክልል ሸማቾች መብት ጥበቃ ማኅበራትን ያቀፈ በሀገር አቀፍ ደረጃ በቦርድ የሚመራ ‘የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ጥበቃ ማኅበራት ጥምረት’ መቋቋሙን ገልጸዋል።
አጠቃላይ ስለጥምረቱ ዝርዝር መረጃም በዓለም አቀፍ የሸማቾች ቀን ይፋ ይሆናል ብለዋል።
የጥምረቱ እውን መሆን እንደ ሀገር የሸማቹን ማሀበረሰብ መብትና ጥቅም በተደራጀ አግባብ ለማስከበር የላቀ ጠቀሜታ የሚኖረው መሆኑን አስረድተዋል።
በሚኒስቴሩ የፀረ ንግድ ውድድርና የሕግ ጥሰት መከላከል ዴስክ ሃላፊ ጌትነት አሸናፊ፤ በሸማቹ ማህበረሰብ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ለመፍታት ክትትልና ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
በሶስተኛው ሩብ ዓመት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ጉድለት ያለባቸው የንግድ ዕቃዎችን የገዙ ሸማቾችን አቤቱታ ምላሽ መስጠት መቻሉን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም የሸማቾችን መብትና ጥቅም የሚጥሱ ድርጊቶችን ለሸማች መብት ጥበቃ ማኅበራት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመጠቆም መብታቸውን እንዲያስከብሩ አስገንዝበዋል።