በኢትዮጵያና በካናዳ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማሳደግ ይገባል-የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና በካናዳ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማሳደግ ይገባል-የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና በካናዳ መካከል ያለውን ዘርፈ ብዙ የሁለትዮሽ ግንኙነት ማሳደግ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ከካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የፓርላማ ፀሐፊ ሮበርት ኦሊፋንት ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅትም አምባሳደር ታዬ ካናዳ የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ወዳጅ መሆኗን ገልጸው፣ ነባር እና ዘርፈ ብዙ የሆነውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ የሁለቱን ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ በመግለጽ የካናዳ ባለሀብቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ፣ በማዕድን፣ በኢነርጂ እና በማምረቻው ዘርፎች መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል።
የካናዳ የፓርላማ ፀሐፊ ሮበርት ኦሊፋንት በበኩላቸው ኢትዮጵያ በካናዳ የውጭ ግንኙነት ውስጥ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።
ካናዳ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በሰብዓዊ ርዳታ፣ በልማት ትብብር እና በሌሎችም ዘርፎች ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አምባሳደር ታዬ ከተከበሩ ሮበርት ኦሊፋንት ጋር በቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችም መክረዋል።