በዞኑ 28 ሺህ 300 ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተከናውኗል--መምሪያው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ 28 ሺህ 300 ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ተከናውኗል--መምሪያው

ደሴ፤ መጋቢት 5 ቀን 2016 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን በዚህ ዓመት የበጋ ወራት ከ28 ሺህ 300 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ መከናወኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለፀ።
በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ መገርሳ ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የበጋ ወራት 59 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም ህብረተሰቡን በብዛት በማሳተፍ በዞኑ የተራቆቱ ተራራማ፣ ገደላማ፣ የቦረቦርና ሌሎችንም አካባቢዎች በማልማት ጠቀሜታ እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ገልጻዋል፡፡
ልማቱ ካለፈው ጥር 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ እስካሁን በ15 ወረዳዎች 28 ሺህ 305 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በስራው ከ355 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ያሉት ቡድን መሪው፤ ከ7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የጉልበት ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።
እቅዱን ለማሳካት የልማት ስራው እስከ ግንቦት ወር 2016 ዓ.ም እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
ቀደም ሲል በተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ስራ የተመናመነውን ደን መልሶ ለመተካት፣ የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ፣ በተፋሰሶች ውስጥ ለንብ ማነብ፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ለእንስሳት ማድለብ ሥራዎች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አብራርተዋል።
የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራም በዞኑ በተመረጡ 796 ተፋሰሶች ላይ እየተከናወነ ሲሆን ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር በሚችል መልኩ እንዲከናወን የባለሙያ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ይገኛል፡፡
የተሁለደሬ ወረዳ የ08 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይማም በለጠ በበኩላቸው፤ በየዓመቱ በሚያከናውኑት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ተጠቃሚ ሆነናል ብለዋል።
የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃው የሰብል ምርታማነት እንዲጨምር ከማድረጉም ባለፈ ከለሙ ተፋሰሶች የእንስሳት መኖን ለማግኘት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተዋል።
ባለፉት ዓመታት የተሰሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የተናገሩት ደግሞ በቃሉ ወረዳ የ03 ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር መሃድ አህመድ ናቸው።
ቀደም ሲል ለዓመታዊ ቀለብ ይቸገሩ እንደነበርና አሁን ላይ የማሳቸው የአፈር ለምነት በመጠበቁ የሰብል ምርታማነትን ማሳደግ በመቻላቸው በሚያመርቱት የተሻለ ምርት የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው ዓመት 43 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መከናወኑንም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡