በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ
ሆሳዕና፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ሰባት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን በክልሉ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተክሌ አሼቦ ፤ ዘንድሮ ከክልሉ ለግድቡ ግንባታ 26 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፉት ሰባት ወራት በተደረገው ርብርብ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸው፤ ገቢውን ከቦንድ ሽያጭና ከልዩ ልዩ ድጋፎች የተገኘ መሆኑን አስረድተዋል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየደረጃው የሚገኘው ማህበረሰብ በዓይነትና ገንዝብ ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ አሁን ቀጥሎ እንዳለ ተናግረዋል።
በዚህም በገንዘብ ከክልሉ ከ388 ሚሊዮን ብር በላይ መዋጮ መደረጉንም አውስተዋል።
በመጪው መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም 13ኛ ዓመቱን የሚይዘው የግድቡ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበት ቀን ድጋፍ ላደረጉት አካላት ዕውቅና የመስጠትና ተጨማሪ ገቢ የማሰባሰቢያ ህዝባዊ ንቅናቄ መርሃ ግብር መዘጋጀቱንም አቶ ተክሌ ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ መአዛ ጥበበወርቅ፤ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ አልምተን መጠቀም ከቻልን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ መምጣት እንደምንችል ታላቁ ህዳሴ ግድብ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ለግድቡ ግንባታ ሁለት ዙር የቦንድ ግዥ መፈፀማቸውን ጠቅሰው አሁንም ለመደገፍ መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግንባታ የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ያጠናከረ የትውልዱ ልዩ አሻራ ነው ያለው ደግሞ ሌላው የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ ወጣት አሳምነው ወንድወሰን ነው።
ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ የሚውል ከዚህ በፊት ቦንድ ከመግዛት ሌላ በማህበራዊ የትስስር ገፆችና በሌሎች ዘዴዎች ድጋፉ እንዲጠናከር ሲያበረታታ መቆየቱን አስታውሶ፤ ይህንን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።