ቀጥታ፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚያከናውኗቸው የልማት ተግባራት ክትትል እና ድጋፍ እንደሚፈልጉ ተጠቆመ

አሶሳ፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የህብረተቡን ችግሮች ለመፍታት የሚያከናውኗቸውን የልማት ተግባራት በሚገባ መከታተል እና መደገፍ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

10ኛው የኢፌዴሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የክልል እና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የጋራ ጉባዔ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ የተጀመረው ሁለንተናዊ ሪፎርም የዜጎችን የመደራጀት መብት እንዲከበር ያስቻለ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ፈተናዎችን በመቋቋም ዕዳን ወደ ምንዳ የመቀየር ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ሂደት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ሃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ሰለሆነም የፌዴራል እና የክልል ባለድርሻ አካላት በእነዚሁ ድርጅቶች የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን በመከታተል እና በመደገፍ ውጤታማ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡



 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ እንደተናገሩት፤ የክልሉ መንግስት የሚነድፋቸው የልማት እቅዶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የጋራ ርብርብ ይጠይቃል፡፡

በዚህ ሂደት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እገዛ እና ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ የክልሉ መንግስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲጠናከሩ አዋጅ አውጥቶ ተግባራዊ ማድረጉንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

የመንግስት እና የሲቪል ማህበራት ጥምረት እና ስልታዊ አጋርነት የህዝብን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መመለስና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማስፈን እንደሚያስችል ጠቁመው፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡


 

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሂ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በክልሉ በዘንድሮው በጀት ዓመት 35 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሶስት ቢሊዮን በሚጠጋ ብር 63 የልማት ፕሮጀክቶች እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ጤና፣ ትምህርት፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ማስፋፋት እና የሴቶች እና ህጻናት ተጠቃሚነት ማጎልበት ድርጅቶቹ የክልሉን መንግስት ጥረት እየደገፉ ከሚገኙባቸው ዘርፎች መካከል እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

እስከ ነገ በሚቀጥለው በዚሁ ጉባዔ የተለያዩ ክልሎች ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመራር አባሎች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም