ለአገራዊ ምክክሩ ተፈጻሚነት ሁሉም የራሱን አሻራ ሊያሳርፍ ይገባል- ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ - ኢዜአ አማርኛ
ለአገራዊ ምክክሩ ተፈጻሚነት ሁሉም የራሱን አሻራ ሊያሳርፍ ይገባል- ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ
ጂንካ ፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦ በአገራዊ ምክክሩ ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት በሚካሄደው እንቅስቃሴ ሁሉም ዜጋ በመሳተፍ የራሱን አሻራ ሊያሳርፍ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ አስገነዘቡ።
ኮሚሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን በአጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ የማህበረሰብ ተወካዮችን እያስመረጠ ነው።
በዚህ ወቅት ፕሮፌሰር መስፍን ባስተላለፉት መልዕክት አገራዊ የምክክር ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ሁሉም ዜጋ የኔ የሚላት አገር ለመገንባት ወሳኝነት እንዳለው ገልጸዋል።
ይህም ለአገራዊ ችግሮቻችን ሀገር በቀል መፍትሄ የምናመነጭበት ታሪካዊ ክስተት ነው ብለዋል።
በምክክሩ ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት በሚካሄደው እንቅስቃሴ ሁሉም ዜጋ በመሳተፍ የራሱን አሻራ ሊያሳርፍ ይገባል ሲሉ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ አስገንዝበዋል።
በተለይ የማህበረሰብ ተወካዮች የህብረተሰቡን አጀንዳ በትክክል ለኮሚሽኑ በማቅረብ መፍትሄ እንዲያገኝ በትጋት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል ።
በአሪ ዞን ከአራት ወረዳዎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች ማህበረሰቡን በመወከል ለምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳ የሚያቀርቡ ተሳታፊዎችን ለመምረጥ ትናንት የተጀመረው መድረክ ዛሬ ማምሻውን ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።