የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የአስር ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ሚያዚያ 13/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢንዳስትሪ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ገለጹ።
ሁለቱ ተቋማት የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የ2016 ዓ.ም የአስር ኪሎ ሜትር ሩጫን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫው ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ፥ የአምራች ኢንዱስትሪ ለአገር እድገትና ብልጽግና አይተኬ ሚና ስላለው መንግስት ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ2014 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለያዩ ከተሞች በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ንቅናቄው የተዘጉ ኢንዱስትሪዎችን እንዲከፈቱ በማድረግ በግሉ ዘርፍ እና በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እመርታዊ ለውጥ እንዲመዘገብ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖዎች ንቅናቄን ለማጠናከርም የ2016 የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ እና የአስር ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር በመጪዎቹ ወራት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው በሚያዚያ 13/2016 ዓ.ም መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ እንደሚካሄድ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ደግሞ ከግንቦት 1 እስከ 5/2016 ዓ.ም በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች በሁለቱም ፆታ በቅደም ተከተል 250 ሺህ ብር፣ 150 ሺህ ብር፣ 100 ሺህ ብር፣ 50 ሺህ ብር እና የ25ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከት አስታውቀዋል።
በክለብ ደረጃም ከ1 እስከ 3 የሚወጡ ተወዳዳሪዎች የ100 ሺህ ብር፣ የ75 ሺህ ብር እና የ50 ሺህ ብር ሽልማት ያገኛሉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የተሳትፎና የውድድር ዳይሬክተር አስፋው ዳኛው፥ ባለፈው ዓመት በእንጦጦ የተካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት የ2016 ዓ.ም የሩጫ ውድድር ስኬታማ እንደነበር አስታውሰዋል።
በዚህ ዓመትም ስኬታማ ውድድር ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፥ በውድድሩም በሁለቱም ፆታ ተሳታፊ ለሆኑ አትሌቶች የተሻለ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆ መፍታት፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች ማስተዋወቅ፣ ዘላቂ የንግድ ትስስር መፍጠር፣ አዳዲስ ባለሃብቶችን ወደዘርፉ መሳብ እና ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የ2016 ዓ.ም ንቅናቄ ዋነኛ ዓላማ መሆናቸው ተመላክቷል።