የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ስብራቶችን ለመጠገን እድል የሚሰጥ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦ ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል እንደ ሀገር ሁለት ስብራቶችን ለመጠገን ትልቅ እድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት “ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል መርቀው በከፈቱበት ወቅት ነው።

የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የሀገርን ስብራቶች ለመጠገን በአዲስ አበባ ከተገነቡ ፕሮጀክቶች ሁሉ የተለየና የላቀ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሀገር ያሉብንን ሁለት ስብራቶች ለመጠገን ትልቅ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

አንደኛው ስብራት ባሉብን ዘርፈ ብዙ ድካሞች ለጎዳና ህይወት የተዳረጉ ልጆችን መልሶ የህይወት መስመራቸውን ማቅናት የሚያስችልና ስብራትን የሚጠግን ነው ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በየዓመቱ 10 ሺህ ሴቶችን ከተመሰቃቀለ ህይወት በማውጣት ኑሯቸውን ማሻሻል የሚያስችል መሆኑ የስብራት መጠገን ሂደቱን ያፋጥናል ነው ያሉት።

ማዕከሉ እውን እንዲሆን የመሪነት ሚናውን ለተወጡት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባና የግንባታ ኮሚቴ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመስግነዋል።

ሁለተኛው ስብራት የስክነትና ማስተዋል አለመኖር እንዲሁም ማሰብና አሻግሮ ማየት አለመቻል መሆኑን ጠቅሰው ይህም ለብዙ ችግሮች መዳረጉን ገልጸዋል።

ሴቶች ከውድድር ይልቅ ትብብርን፣ ከግልፍተኝነት ይልቅ ማስተዋልን፣ የእርቅና የሰላም መንፈስን የሚሞሉ ስለመሆናቸውም አንስተዋል።

ባልተገባ ህይወት ጎዳና ላይ ወጥተው የሚኖሩ ሴቶች መኖራቸው እንደ ሀገር ስብራቱን እንደሚያሰፋው በመጠቆም፤ለነገዋ ማዕከል ከጎስቋላና ካልትገባ የህይወት ሂደት ወጥተው በተሻለ ሁኔታ እንዲኖሩ በማድረግ ስብራትን ለመጠገን ሚናው የላቀ መሆኑን አስረድተዋል።

ሴቶች እንደ ሀገር ግማሽ ያህሉን ስራ በማከናወን የላቀ አበርክቶ እንዳላቸው ገልጸው እነሱን ማነፅ፣ ማስተማርና ማብቃት ካለተቻለ ሀገራዊ ግብን ማሳካት አይቻልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ በብዙ ነገሮች ወደ ኋላ መቅረቷን አንስተው ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር መፍጠን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ የከተማነት ደረጃ ወደ ኋላ ከቀሩ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን የተጀመረው ስራ በጥቂት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባን በአፍሪካ ቀዳሚዋ ውብና ለዜጎች የተመቸች ከተማ የሚያደርግ ነው፤ ይህንንም ሰርተን እናሳያለን ነው ያሉት።

ለዚህም በከተማዋ በርካታ መሰረተ ልማቶች፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሚናቸው የላቀ ተቋማት እየተገነቡ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ለከተማዋና ለሀገር ሁለንትናዊ ለውጥ ሁሉም ዜጋ አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም