“ለነገዋ” የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በችግር ላይ ለሚገኙ ለሴቶች አዲስ የህይወት ምዕራፍ የሚከፍት ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
“ለነገዋ” የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በችግር ላይ ለሚገኙ ለሴቶች አዲስ የህይወት ምዕራፍ የሚከፍት ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦ “ለነገዋ” የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በችግር ላይ ለሚገኙ ሴቶች አዲስ የህይወት ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሕመድ(ዶ/ር) “ለነገዋ” የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከልን መርቀው ከፍተዋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የማዕከሉ መገንባት የሴቶችን እኩልነትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የላቀ ሚና አለው ብለዋል።
በሴቶች ላይ የሚደርስ ፆታዊ ጥቃት ለማህበራዊ በደሎች ከማጋለጥ በላይ ለማህበረሰባቸውና ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዳያበረክቱ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ምክንያቶች ለማህበራዊ ችግሮችና ለወሲብ ንግድ የተጋለጡ ሴቶችን ተሃድሶ በመስጠት መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ማእከል መገንባቱን ገልጸዋል።
ከዚህ አኳያ ማዕከሉ የተሻለ ነገን፣ ብሩህ ተስፋን፣ ፅናትና የሰርቶ የመለወጥ እድልን የመትከል ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።
አቅም በፈቀደ መልኩ ለሴቶች እኩል ተጠቃሚነት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን አበረታች ውጤቶችም እየተመዘገቡ መሆኑን ነው የተናገሩት።
አሁንም በርካታ ሴቶች ለኢኮኖሚ ጥገኝነትና ለአካላዊ ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሰው ማዕከሉ ሁሉንም ችግሮች የሚፈታ ባይሆንም ለበርካቶች ተስፋ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ለጎዳና ህይወትና ለወሲብ ንግድ የተጋለጡ ሴቶች ራሳቸውን ችለው ወደ ኢኮኖሚ እንዲገቡ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ማእከሉ መሰረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል።
ማዕከሉ በብዙ ዘርፎች የተደራጀ ሲሆን በዓመት በአራት ዙሮች ሴቶችን በማሰልጠን በቂ ተሃድሶ አግኝተው ወደ መደበኛ ህይወት እንዲገቡ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል።
በማዕከሉ የተሃድሶ ስልጠና የሚሰጥባቸው የክህሎት ማበልፀጊያ፣ የማሰልጠኛ ማዕከላት፣ የስነ ልቦና እና የምክር አገልግሎት፣ የህክምና፣ የመመገቢያ አዳራሾች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የመዝናኛና ሌሎችንም ስፍራዎች ያካተተ ነው።
በዓመት እስከ 10 ሺህ ሴቶች የተለያዩ የሙያና ክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚያግዝም ነው።