የቻይና- አፍሪካ የንግድ ልውውጥ ዕድገት  

737

የቻይና አፍሪካ ግንኙነት ባለፉት አስርት አመታት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ በመምጣቱ ቻይና በአፍሪካ አህጉር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ዋነኛ ተዋናይ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ አድርጓታል። 

በቻይና እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ከ47 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን የስፑትኒክ ዘገባ ያመለክታል። የንግድ ልውውጡ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ብቻ በ13.9 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።  

ቻይና ወደ አፍሪካ የምትልከው ምርት በ21 በመቶ ማደጉን ያመለከተው ስፑትኒክ በአንፃሩ ቻይና ከአፍሪካ ሀገራት የምታስገባው ምርት መጠን በ4.5 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። 

በፈረንጆቹ 2021 ይፋ የሆነው የቻይና አፍሪካ ትብብር ራዕይ 2035፤ "በአፍሪካ የተሰራ" የሚሉ ብራንዶችን በመፍጠር እና በማቋቋም ረገድ የአፍሪካ ምርቶች በዓለም ገቢያ ተመራጭ እንዲሆኑ ቻይና እየሠራች እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል። 

የቻይና አፍሪካ 2035 ራዕይ አፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን እንድታሳድግ እና ከአለም አቀፍ የኢንዱስትሪ እና የአቅርቦት ሰንሰለት ጋር እንድትተሳሰር ለማድረግ እቅድ እንዳለውም በዘገባው ተጠቁሟል።

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ 2023 መገባደጃ ላይ ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት የአፍሪካ ሀገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገሯ እንዲገቡ መፍቀዷን ያስታወሰው ዘገባው፤ ይህም የአፍሪካ ቻይና የንግድ ትስስርንና ትብብርን ከፍ እንዲል አድርጓል ብሏል።

ከአፍሪካ ሀገራት ደቡብ አፍሪካ የቻይና ትልቁ የንግድ አጋር መሆኗን ያመለከተው ዘገባው፤ ናይጄሪያ፣ አንጎላ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንደቅደም ተከተላቸው የቻይና የንግድ አጋር መሆናቸውን መረጃው ያመለክታል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም