የእዝነትና የምህረት ወቅት የሆነውን የረመዳን ወር መልካም ተግባራትን በማከናወን ልንጠቀምበት ይገባል- ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ - ኢዜአ አማርኛ
የእዝነትና የምህረት ወቅት የሆነውን የረመዳን ወር መልካም ተግባራትን በማከናወን ልንጠቀምበት ይገባል- ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦የእዝነትና የምህረት ወቅት የሆነውን የተከበረውን የረመዳን ወር መልካም ተግባራትን በማከናወን ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ገለጹ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የኢፍጣር መርሐ-ግብር አካሂዷል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና የኢትዮጵያ ኃማኖቶች ጉባኤ ተወካዮች ተገኝተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ የእዝነት የምህረትና የመረዳዳት ወቅት የሆነውን የረመዳን ወር መልካም ተግባራትን በማከናወን ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ የኢፍጣር መርኃ ግብርም ይህንን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ሕዝበ ሙስሊሙ ሁሌም የሚተገብራቸው መልካም ተግባራት መኖራቸውን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ በረመዳን ወር ግን መልካም ስራዎች የተለየ ዋጋ የሚሰጣቸው በመሆኑ ልንተጋ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም በተከበረው የረመዳን ወር የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተጣላን በማስታረቅና ሌሎች መልካም ተግባራትን በማብዛት እናሳልፍ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ የፕሬዝዳንት ልዩ አማካሪ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፤ የረመዳን ወር የተበላሸን በማስታካከል አዲስ የህይወት ምዕራፍ የምንማርበት የተቀደሰ ወቅት ነው ብለዋል።
በመሆኑም ይህንን ታላቅ ዋጋ የሚገኝበትን ወር በመረዳዳት፣ በመተጋገዝና ሌሎች መልካም ተግባራትን በማብዛት ማሳለፍ አለብን ብለዋል።