በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ 

765

ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የነዳጅ ፍጆታ ለመቀነስ እና የአየር ብክለትን ለመከላከል የሚደረገውን ሰፊ ጥረት እውን ለማድረግ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለህዝብ ማመላለሻ አገልግሎት በማዋል ከፍተኛ እምርታን አስመዝግባለች ይላል የአፍሪካ 24 ድረ ገጽ ዘገባ። 

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እየተዘዋወሩ የሚገኙት የኤሌክትሪክ ሚኒባሶች ድምጽ አልባና ለአካባቢው ተስማሚ መሆናቸውን ያተተው የአፍሪካ 24 ድረ ገጽ ዘገባ፤ ይህ የለውጥ ጅማሮ እየጨመረ በመጣው ፍላጎት እና በመንግስት ጠንካራ ድጋፍ የተገኘ መሆኑን አመልክቷል። 

መንግስት በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በረጅም የጊዜ ማእቀፍ ውስጥ ከጎዳናዎች የማስወጣት እቅድ ነድፎ እየሰራበት በመሆኑ ምክንያት አሮጌዎቹን የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ተክተው ለዜጎች ንጹህና ጤናማ አገልግሎት የሚሰጡት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከፍ ያሉ ማበረታቻዎች እየተደረገላቸው መሆኑንም ዘገባው አመልክቷል።

ከእነዚህ ማበረታቻዎች መካከልም ለአካባቢ ጥበቃና ለጤና ምቹ ናቸው የተባሉት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ያለምንም ቀረጥ አሊያም በዝቅተኛ ቀረጥ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ወይም በከፊል ገብተው እንገጣጠሙ ማድረግ ተጠቃሽ ነው።

እነዚህ ተሽከርካሪዎች ሃገር ውስጥ ገብተው መገጣጠማቸው ለኢትዮጵያውያን የእውቀትና የሙያ ሽግግር ከማድረጋቸው ባለፈ ለወጣት ክፍል የስራ እድሎችን እንደሚፈጥሩ ዘገባው አመልክቷል።

በሃገር ውስጥ የተገጣጠሙት ተሽከርካሪዎች የዜጎችን እንቅስቃሴ ከማሳለጥ አኳያም ጉልህ አበርክቶ እንዳላቸውም ጠቁሟል። 

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መስፋፋት ለነዳጅ ግዥ የሚወጣውን ከፍተኛ የሃገር ሃብት ለሌላ ልማት ለማዋልና ከአካባቢ ጥበቃና ከዜጎች ጤና ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት መሆኑን ያነሳው ዘገባው ተሽከርካሪዎቹ በስፋት ጥቅም ላይ ሲውሉ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻላቸውም ባሻገር ጤናማ የከተሞች ውስጥ እንቅስቀሴ በመፍጠር የአረንጓዴ አሻራ ትልሙን በማሳካት ያግዛሉ ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም