ቀጥታ፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአቶ ክርስቲያን ታደለን ያለመከሰስ መብት አነሳ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2016(ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአቶ ክርስቲያን ታደለን ያለመከሰስ መብት አነሳ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባ የአቶ ክርስቲያን ታደለን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።


 

የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፤ ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ ተጠርጣሪው በአማራ ክልል ተደራጅቶ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ከሚንቀሳቀሰው ፀረ-ሰላም ኃይል ጋር ትስስር ያለውና ለዚሁ ቡድን መመሪያ ሲሰጥ ነበር ብለዋል።

የፀረ-ሰላም ኃይል በማደራጀት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ትዕዛዝ ሲሰጥ እንደነበር የቀረቡ ማስረጃዎች እንደሚያስረዱም ነው የገለጹት።

የተጠርጣሪው ድርጊት የሽብር አዋጅን ለመከላከል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 እንዲሁም በወንጀል ሕጉ የሚያስከስስ ከባድ ወንጀል መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም በተጠርጣሪው ላይ ፍርድ ቤት ክስ ማቅረብ እንዲችል የተጠርጣሪውን ያለመከሰስ መብት ማንሳት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የተጠርጣሪውን ያለመከሰስ መብት ማንሳትን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ጥያቄና አስተያየቶች ተሰጥተዋል።

የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በምላሽና ማብራሪያቸው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብትን ጨምሮ በርካታ ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት የተገደበ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም መሠረት የምክር ቤት አባላቱ ፈቃድ ሳይጠየቅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማዕቀፍ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብለዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጠርጣሪዎች በልዩ ፍርድ ቤትና ልዩ ሥርዓት ጉዳያቸው እንዲታይ ማድረግ እንደሚቻል አንስተው፤ ተጠርጣሪዎች የተሻለ ራሳቸውን የመከላከል መብት እንዲያገኙ ለማድረግ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን መውሰድ ይገባል ሲሉ አስረድተዋል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ያፀደቀ ሲሆን፤ ሁለት ረቂቅ አዋጆችንም ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል። 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም