የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ይጀመራሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ይጀመራሉ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።
በድሬዳዋ ስታዲየም በሚካሄደው ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ 10 ሰዓት ይገናኛሉ።
ባህር ዳር ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ በሁለት ጨዋታ ተሸንፎ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በደረጃ ሰንጠረዡም በ26 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል፤ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
ኢትዮጵያ ቡና በ29 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሌላኛው 18ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ ሀምበሪቾ ዱራሜ ከአዳማ ከተማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ተሳትፎውን እያደረገ የሚገኘው ሀምበሪቾ ዱራሜ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በአራቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ክለቡ በ7 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዞ ይገኛል።
ተጋጣሚው አዳማ ከተማ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በአንዱ ሲሸነፍ በሶስቱ አቻ ወጥቷል፤ በ24 ነጥብም 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የፕሪሚየር ሊጉ የ18ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ድሬዳዋ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት፤ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደረጃ ሰንጠረዡ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው መቻል ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ መጋቢት 8 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሊጉን በ36 ነጥብ እየመራ ይገኛል።