በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበት ዓመት ለማክበር ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች ይከናወናሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበት ዓመት ለማክበር ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች ይከናወናሉ
አሶሳ ፤መጋቢት 4/2016(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበትን 13ኛ ዓመት በዓል በቦንድ ሽያጭ፣ በተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤና የልማት እንቅስቃሴ እንደሚከበር በክልሉ የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
የክልሉ የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግራኝ ጉደታ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የግድቡ ግንባታ መሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተለያዩ መረሃ ግብሮች ይካሄዳሉ።
ከመረሃ ግብሮቹም መካከል ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ የሚውል የቦንድ ሽያጭ እንደሚገኝበት ጠቅሰው፤ ከዚህም ስድስት ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
ክልሉ የብድር እና ቁጠባ ተቋማት፣በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ልማት ባንክ ቅርንጫፎች በኩል የቦንድ ሽያጭ እንደሚያከናወን ጠቁመዋል፡፡
ህብረተሰቡ የበጋ ተፋሰስ ልማትን ጨምሮ የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ በማጠናከር የህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት 13ኛ ዓመት እንደሚከበር አስታውቀዋል።
የክልሉ ነዋሪዎች የህዳሴው ግድቡ ውሃ መያዝ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በገንዘብ ድጋፍ፣ በደን ምንጣሮና በፕሮጀክቱ ስራ ሲሳተፍ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በዚህም የስራ እድል ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አብራርዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ሠራተኞች፣ ባለሃብቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ አርሶ አደሮች እና ሌሎችም በቦንድ ግዥው በመሳተፍ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ አቶ ግራኝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እስካሁን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ112 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ጨምረው ገልጸዋል፡፡