በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን መካከል ያለው የሁለትዮሽ የትብብር ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል- አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን መካከል ያለው የሁለትዮሽ የትብብር ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል- አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ
አዲስ አበባ ፤መጋቢት4/2016(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን መካከል ያለው የሁለትዮሽ የትብብር ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ተናገሩ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ጋር ተወያይቷል።
የውይይታቸው ትኩረትም የሁለቱን አገራት ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ነው።
በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የቆየ የትብብር ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል በተለይም በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና ሌሎችም ዘርፎች ጠንካራ ትስስር መኖሩን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓኪስታን ካራቺ በሳምንት አራት ጊዜ በረራ ማድረጉ በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል ንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጓልም ነው ያሉት።
በመሆኑም በቀጣይነት የሁለቱን አገራት ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ፓኪስታን ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ኖጎ፤ በኢትዮጵያና ፓኪስታን መካከል የቆየ ወዳጅነት መኖሩን አንስተዋል።
በመሆኑም የሁለቱን አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነትና ወዳጅነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረናል ብለዋል።
የሁለቱን አገራት ፓርላማዎች ግንኙነት በማጠናከር በጋራ በመስራት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ለማጠናከርም እንዲሁ።
የኢትዮጵያና ፓኪስታንን የሁለትዮሽ ግንኙነት በላቀ መልኩ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ሥራዎች በሁለቱም አገራት ዘንድ እየተከናወኑ መሆኑ ይታወቃል።