ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን በሎጂስቲክስ አገልግሎት ተወዳዳሪ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ ፤መጋቢት4/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያን በሎጂስቲክስ አገልግሎት ተወዳዳሪ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የግል ደርጅቶችን ተሳትፎ ለማጠናከር አስፈላጊው እገዛ የሚደረግ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር  ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።       

የመልቲ ሞዳል ሎጂስቲክስ አገልግሎት አሰራር በአንድ የስምምነት ሰነድ አንድን ዕቃ በመርከብ፣ በአየር በየብስና ባቡርን በመሳሰሉ አማራጮች ከመነሻ እስከ መድረሻ የሚጓጓዝበት ነው። 

አሰራሩ የተቀናጀ በመሆኑ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ከመቀነስ ባለፈ የጊዜ ብክነትንም የሚያስቀር ዘመናዊ አሰራር መሆኑ ይታወቃል።

 በመሆኑም በመልቲ ሞዳል ሎጂስቲክስ አገልግሎት የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ በሚያስችለው መመሪያ መሰረት ብቁ ለሆኑ ድርጅቶች ፈቃድ መስጠት ተጀምሯል።    

በዛሬው ዕለትም ባስመዘገቡት ካፒታል፣ በሰው ኃይል፣ ባላቸው መሳሪያ፣ መጋዘኖችና መስሪያ ቦታዎች ብቁ ሆነው ለተገኙ ድርጅቶች ፈቃድ ተሰጥቷል።

በዚህም መሰረት ፓናፍሪክ ግሎባል ሎጂስቲክስ፣ ጥቁር አባይ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት እንዲሁም ኮስሞስ መልቲ ሞዳል ሼር ካምፓኒ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል።    

 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፤ በሎጂስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

  በመልቲ ሞዳል አሰራር የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ ውጤታማነትን ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በሎጂስቲክስ አገልግሎት ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ለማድረግ የግል ደርጅቶችን ተሳትፎ ለማጠናከር አስፈላጊው እገዛ ይደረጋል ብለዋል።

በተለይም በመልቲ ሞዳል የሎጂስቲክስ አገልግሎት ላይ አቅሙ ያላቸው ድርጅቶች እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ፤ የመልቲ ሞዳል ሎጂስቲክስ አገልግሎት በኢትዮጵያ በአማካይ እስከ 20 ሚሊዮን የሎጂስቲክስ ወጪ መቀነስ የሚያስችል መሆኑ ተለይቷል።   

በዚህም የግሉ ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

የጥቁር አባይ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰኢድ እንድሬ፤ በመልቲ ሞዳል ሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመሳተፍ በቂ ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።

በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም የተቀላጠፈ የአሰራር ስርአት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቱ ቀደም ብሎ መጠናቀቁን ገልጸዋል።


 

የፓናፍሪክ ግሎባል ሎጂስቲክስ ደርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤልሳቤጥ ጌታሁን፤ በዘርፉ ልማት ተሳታፊ መሆናቸው ሀገርና ህዝብን ለማገልገል ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።  

በመልቲ ሞዳል የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመስጠት ብቁ ሆነው ለተገኙ የግል ድርጅቶች በእለቱ የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም