ቀጥታ፡

በኢትዮጵያና በፓኪስታን መካከል ያለው ሁለንተናዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና በፓኪስታን መካከል ያለው ሁለንተናዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ የግንኙትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጿል።

ይህ የተገለጸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከፓኪስታኑ አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ጋር በሁለቱ ሀገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ዙሪያ በተወያዩበት ወቅት ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ እና የፓኪስታን ሁለንተናዊ ትስስር ታሪካዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንዲረዳ ሁለቱም ሀገራት ኤምባሲዎቸቸውን ከፍተው እየሰሩ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች በንግድ፣ በጤና፣ በኢንቨስትመንት፣ በባህል እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር በማስተሳሰር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ሚያን በበኩላቸው በኢትዮጵያና ፓኪስታን መካከል ያለውን ንግድና ኢንቨስትመንት፣ የትምህርት፣ የኢኮኖሚ፣ የባህልና ቱሪዝም እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ትስስር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በትምህርት፣ በጤናና በኢንቨስትመንት ልማት ዘርፍ የፓኪስታን ባለሃብቶች እንዲሁም ሙሁራን በስፋት እየሰሩ እንደሚገኙም ገልጸው፤ በቀጣይነትም ይህን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራም አምበሳደሩ ጠቁመዋል።

የሁለቱን ሀገራት የፓርላማዎችና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንዲረዳ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔዎች ፓኪስታን ተገኝተው ከፓኪስታን የፓርላማ አባላት ጋር የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ መግለጻቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም