ሀገራዊ ምክክሩ በዘመናት መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ያደርጋል--ዶክተር ዮናስ አዳዬ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ በዘመናት መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ያደርጋል--ዶክተር ዮናስ አዳዬ
ጂንካ፤ መጋቢት 4 /2016 (ኢዜአ)፡-ሀገራዊ ምክክሩ በዘመናት መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ስለሚያደርግ ዜጎች በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ አስገነዘቡ።
ኮሚሽኑ በዛሬው ዕለት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን በአጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ የማህበረሰብ ተወካዮችን እያስመረጠ ነው።
በዚሁ ጊዜ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ እንዳሉት ሀገራዊ የምክክር ሂደት በዘመናት መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች ተፈትተው ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው።
ሂደቱ አሳታፊና ሁሉንም ዜጋ ማዕከል ባደረገ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ የተሳካ እንዲሆንም ዜጎች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
"በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት ልዩነቶችን ለማጥበብ ጥረት ማድረግ ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል" ሲሉም አመልክተዋል።
ዶክተር ዮናስ እንዳሉት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ እየተካሄደ ያለው የምክክር ሂደት ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ወሳኝ ነው።
በመሆኑም ምሁራን፣ ዜጎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የሲቪክ ማህበራት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኮሚሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከማህበረሰቡ አጀንዳ በመውሰድ ለምክክር ኮሚሽኑ የሚያቀርቡ የማህበረሰብ ተወካዮችን እያስመረጠ መሆኑንም ዶክተር ዮናስ ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለትም ኮሚሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን በአጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ የማህበረሰብ ተወካዮችን ምርጫ እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በምርጫው በአሪ ዞን የሚገኙ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ መምህራን፣ አርሶ አደሮች፣ የማህበረሰብ መሪዎች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ የእድሮች እና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።