ሶስት አገር በቀል ኩባንያዎች መልቲ ሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ፈቃድ አገኙ - ኢዜአ አማርኛ
ሶስት አገር በቀል ኩባንያዎች መልቲ ሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ፈቃድ አገኙ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት4/2016(ኢዜአ)፦ ሶስት አገር በቀል ኩባንያዎች መልቲ ሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ፈቃድ አገኙ።
ድርጅቶቹ የብቃት ማረጋገጫ እውቅና የምስክር ወረቀት ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ እጅ ተቀብለዋል።
ፓናፍሪክ ግልባል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ፣ ጥቁር አባይና ኮስሞስ መልቲ ሞዳል ሼር ካምፓኒ የመወዳደሪያ መስፈርቱን አሟልተው የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች ናቸው።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ አገልግሎት ተወዳዳሪ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ድርሻ ከፍተኛ ነው ። '
የግል ድርጅቶች የሎጂስቲክስ አገልግሎት እንዲሰጡ የግሉን ዘርፍ የሚያሳትፍ መመሪያ መዘጋጀቱን ጠቁመው በመመሪያው መሰረት ለግል ትራንስፖርት ሰጪ ድርጅቶች ፈቃድ መሰጠት መጀመሩን ገልፀዋል ።
በዛሬው ዕለት የመወዳደሪያ መስፈርቱን ላሟሉ ሶስት ድርጅቶች የተሰጠው ዕውቅና የዛ አካል ነው ያሉት ሚኒስትሩ ዕወቅናና ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አመልክተዋል።
መልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ማለት የአንድን ሀገር የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ከመነሻ ሀገር እስከ የዕቃው መዳረሻ በአንድ ሰነድ /በባህር፣ በየብስና የአየር/ አይነቶችን ተጠቅሞ ጭነቶችን የሚያጓጉዝ የትራንስፖርት አይነት ነው፡፡