ባለፉት ስድስት ወራት ለ14 ሺህ ከስደት ተመላሾች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስድስት ወራት ለ14 ሺህ ከስደት ተመላሾች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል
አዳማ ፤መጋቢት 4/2016(ኢዜአ)፦ ባለፉት ስድስት ወራት ስልጠና ከወሰዱ 32 ሺህ ከስደት ተመላሾች መካከል 14 ሺህ የሚሆኑትን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለጸ።
ፍትህ ሚኒስቴር ከፌዴራልና ክልል የፍልሰት ትብብር ጥምረት አባል ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ከፌዴራል ፖሊስ ስራ አመራር አባላት ጋር በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በአዳማ ከተማ መክረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የስደት ተመላሾችን የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተካሄዱ ባሉት ተግባራት ዙሪያ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊን አነጋግሯል።
ከስደት ተመላሾቹ ከደረሰባቸው አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እንዲሁም ሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያገግሙበት ሥልጠና እየተሰጣቸው መሆኑም ተገልጿል፡፡
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የስራ ስምሪት ማስፋፊያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሰፋ ፈረደ በጉዳዩ ላይ እንዳሉት ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋምና የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው የልማት ተሳታፊ ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
በዚህም በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው አጋማሽ ከ31 ሺህ በላይ ከስደት ተመላሾች ተለይተው በሀገራቸው ሰርተው መለወጥ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መውሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡
ስልጠናውን ከወሰዱት መካከል 14 ሺህ የሚሆኑት ስልጠና ወስደው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ 17ሺህ ወገኖች ደግሞ ወደ ሥራ የሚያስገባቸው የሙያ ስልጠና ማጠናቀቃቸውን አቶ አሰፋ ገልጸዋል፡፡
ከስደት ተመላሾቹ ሥራ ከጀመሩባቸው መስኮች መካከል የፀጉርና ውበት ሙያ፣ ከተማ ግብርና፣ ሳሙናና ውበት መጠበቂያ ምርቶችና ዕደ ጥበብ እንደሚገኙበት አመልክተዋል፡፡
ለስደት ተመላሾቹ የተፈጠሩት የሥራ ዕድሎቹ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከማሳደግ ባለፈ፣ በሀገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ መሆኑን አሳይተዋል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ በቀጣይም ለሌሎች ከስደት ተመላሾች ስልጠና በመስጠት ሰርተው ራሳቸውን የሚለውጡበትን መንገድ እንደሚያመቻች መሪ ሥራ አስፈጻሚው አመልክተዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ ዓሊ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ከስደት ተመላሾች በስደት ላይ ከሚገጥሟቸው ቀውስ የሚያገግሙበትን የሥነ ልቦና ስልጠና በመስጠት የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ከስደት የተመለሱ ከ45 ሺህ በላይ ስደተኞችን ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሥልጠና አግኝተው ሥራ እንዲፈጥሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን አስታውቀዋል፡፡
ከሚኒስቴሩ ጋር በመቀናጀት የተጀመረው እንቅስቃሴ ስደተኞች የሰለጠኑትን ሙያና የሚፈጠርላቸውን የሥራ እድል ተጠቅመው ሀብት ከማመንጨት ባለፈ ለሌሎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ህገወጥ ስደትን ለመቀነስ ድርሻቸውን እንዲወጡ እያገዘ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሕገ ወጥ ስደትና በሰው መነገድን ለመከላከል ዘንድሮ በክልሎች የተጠናከረ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኗ ቀደም ሲል ተገልጿል።