የኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማት ትብብርና ተወዳዳሪነትን የሚያጎለብት ነው- የተሸላሚ ተቋማት አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማት ትብብርና ተወዳዳሪነትን የሚያጎለብት ነው- የተሸላሚ ተቋማት አመራሮች
አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 3/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማት ትብብርና ተወዳዳሪነት የሚያጎለብት መሆኑን የተሸላሚ ተቋማት አመራሮች ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአድዋ ድል መታሰቢያ በተካሄደ ደማቅ ስነ-ስርዓት ለአምስት ተቋማት ‘የኢትዮጵያ ተቋማት ስኬት ሽልማትን’ አበርክተዋል።
ሽልማቱ የተበረከተው ለግብርና ሚኒስቴር በስንዴ ልማት ፕሮግራም ፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለኢትዮጵያ ፖስታ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ነው፡፡
የተሸላሚ ተቋማት አመራሮች እንዳሉት፤ እውቅናው ይበልጥ እንዲሰሩ ከማነሳሳቱም በላይ ለሌሎች ተቋማት አርአያነትን የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፤ ሽልማቱ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን እውቅና የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ሁሉም ተቋማት በተሰማሩበት መስክ ተግተው እንዲሰሩ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው ሽልማቱ ለተቋሙ ስኬት ቀን ከሌት ለሚሰሩ ሰራተኞች ሞራል የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እውቅናው ሌሎች ተቋማትም ስኬታማ ለመሆን እንዲሰሩ በማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ተቋማትን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ተቋሙ ለደንበኞቹ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ሽልማቱ ለተመዘገቡ ስኬቶች እውቅና ከመስጠቱም በላይ በቀጣይ የተሻለ ስራ ለማከናወን መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በስንዴ ልማት የተከናወነው ስራ ተቋማት የተሻለ እቅድ በማዘጋጀትና ሁሉን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ስኬታማ ስራ መከናወን እንደሚቻል አመላካች ነው ያሉት ደግሞ የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ናቸው፡፡
ከዚህ አኳያ ሽልማቱ ለመላ ኢትዮጵያዊያን አርሶ እና አርብቶ አደሮች ጭምር እውቅና የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡