በተቋማት ላይ ተግባራዊ የተደረጉ የሪፎርም ስራዎች ከአገር ባለፈ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ተቋማት እንዲፈጠሩ አስችሏል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በተቋማት ላይ ተግባራዊ የተደረጉ የሪፎርም ስራዎች ከአገር ባለፈ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ተቋማት እንዲፈጠሩ አስችሏል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 3/2016(ኢዜአ)፦ በተቋማት ላይ ተግባራዊ የተደረጉ የሪፎርም ስራዎች ከአገር ባለፈ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ተቋማት እንዲፈጠሩ ማስቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር) በአድዋ ድል መታሰቢያ በተካሄደ ደማቅ ስነ-ስርዓት ለአምስት ተቋማት ‘የኢትዮጵያ ተቋማት ስኬት ሽልማትን’ አበርክተዋል።
ሽልማቱ የተበረከተው ለግብርና ሚኒስቴር በስንዴ ልማት ፕሮግራም፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለኢትዮጵያ ፖስታ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ተቋማቱ እውቅና የተበረከተላቸው ከአገር ባለፈ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችል ስራ በማከናወናቸው ነው፡፡
ስኬት የሚቆም ሳይሆን አዳዲስ ፍላጎቶችን በመያዝ የሚቀጥል ጉዞ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አኳያ ተቋማቱ የተበረከተላቸው እውቅና በቀጣይ ይበልጥ ለመስራት ኃላፊነት የሚሰጥ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ስንዴ በብዛት ከውጭ ከሚያስገቡ የአፍሪካ አገራት አንዷ እንደነበረችም አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተከናወነው ስራ በአፍሪካ ቀዳሚዋ ስንዴ አምራች አገር መሆን መቻሏን ገልጸው፤ የግብርና ሚኒስቴር ለዚህ ስኬት ከፍተኛ ሚና ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቬሽን ዘርፉ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተፈተነበት ወቅት ጭምር ፈተናዎቹን ወደ ስኬት በመቀየር ተወዳዳሪ ተቋም ሆኖ መቀጠል መቻሉን ተናግረዋል፡፡
አየር መንገዱ አሁን ላይ ከአገር ባለፈ አፍሪካን በዘርፉ የሚያስጠራ ግዙፍ ተቋም መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
በቅርቡ እያከናወናቸው ያሉ የአውሮፕላን ግዥ እና የተርሚናል ማስፋፊያ ስራዎችም ተወዳዳሪነቱን ይበልጥ የሚያስቀጥሉ ስለመሆናቸውም አብራርተዋል፡፡
በተመሳሳይ ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞቹን ቁጥር ከእጥፍ በላይ በማሳደግ አሁን ላይ ከ76 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ማፍራት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
የቴሌ-ብር ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥርም 43 ሚሊዮን መድረሱን ጠቅሰው፤ ይህም ተቋሙን በአፍሪካ በርካታ ደንበኞች ካሏቸው ኩባንያዎች ተርታ እንዲሰለፍ አድርጎታል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ለተቋማቱ የተሰጠው እውቅና በቀጣይ በዘርፉ ያሉ አቅሞችን ለመጠቀም መነሳሳትን የሚፈጥር ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
የሪፎርም ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ መሆን የቻለው ሌላኛው ተቋም የኢትዮጵያ ፖስታ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ተቋሙ ከኪሳራ ከመውጣት ባሻገር በአንዳንድ አሰራሮቹ በአህጉር አቀፍ ደረጃ አብነት መሆን መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ከፍተኛ ሚና ማበርከታቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቆሙት፡፡
በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የተከናወኑ የለውጥ ስራዎችም የተቋማት ሪፎርም ውጤታማነት ማሳያ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በዚህም ፈተናዎችን በመቋቋም በግድቡ ግንባታ ሂደት ታሪክ የሚያወሳው አኩሪ ስራ መከናወኑን ነው የገለጹት፡፡
ግድቡ ከኢትዮጵያ ባለፈ የቀጠናው የትስስር ማእከል እንደሚሆንም ነው የተናገሩት፡፡
በቀጣይም ሁሉም ተቋማት በዛሬው እለት እውቅና የተሰጣቸውን ተቋማት አርአያ በመከተል ተግተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡