በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የዜጎች አዎንታዊ ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ የሰላም ተቋም ገለጸ።
የትኛውም ዓይነት ጥያቄ አለኝ ከሚል ኃይል ጋር መንግሥት ሰላማዊ ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም የሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኢትዮጵያ የሰላም ተቋም ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ) ጋር በመተባበር በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ ዓላማ ያደረገ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የኢትዮጵያ የሰላም ተቋም የቦርድ ሊቀመንበር አምባሳደር ሙሉጌታ ኢተፋ (ዶ/ር)፤ የቀደሙት አያቶቻችን በአርበኝነትና በጀብዱ የኢትዮጵያን ነፃነቷን አስጠብቀው አስረክበውናል ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ሰላምና አንድነቷን በማስጠበቅ ልማትና እድገቷን ለማረጋገጥ በጋራ መቆም አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት ሂደት የመንግሥትን ጥረት አድንቀው፤ ሌሎችም ይህንኑ መልካም አርዓያ ሊደግፉት ይገባል ብለዋል።
በተለይም የሃይማኖት አባቶች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች መንግሥትን በማገዝ ለሰላም አበክረው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የዜጎች ጥረትና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
በመድረኩ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፤ የሰላም ግንባታ ሂደት የዜጎችን እገዛና ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያን የረዥም ጊዜ ገናና ታሪክና የአብሮነት እሴት የሚያሳንሱ ችግሮችን በሃሳብ የበላይነት በመፍታት በጋራ ማልማት እንደሚገባም አንስተዋል።
በዚሁም መንግሥት በአማራም ሆነ በኦሮሚያና ሌሎች ክልሎች የተፈጠሩ ችግሮችን በሰላማዊ የምክክር መንገድ መፍትሔ ለመስጠት ጥያቄ አለኝ ከሚል ማንኛውም ኃይል ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሰላም ተቋም የሰላም እጦት በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የሚያስከትለውን ጉዳት በመገንዘብ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ እያደረገ የሚገኘውን አስተዋፅዖ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
በዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ. የዴሞክራሲ እና አስተዳደር ቢሮ ዳይሬክተር ስቴፋኒ ጋርቬይ፤ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ልማትን ለማረጋገጥ በመንግሥት የሚደረገውን ጥረት ድርጅታቸው ያግዛል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የምርምር ዘርፍ ኃላፊ ተባባሪ ፕሮፌሰር ደሳለኝ አምሳሉ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች በዜጎች፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ የከፋ ጉዳት እያስከተሉ ነው ብለዋል።
የሰላምና ፀጥታ ችግሮችን ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የመፍትሔ አማራጮችን መከተል እንደሚገባ አመላክተዋል።
በመድረኩ ላይ በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት እያስከተለ ያለውን ዘርፈ-ብዙ ጉዳት የሚያመላክት የመነሻ ጽሑፍ ቀርቧል።
በመድረኩም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ፤ የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደጀኔ ልመንህ ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።