አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በሕብረተሰብ ጤና የሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሐ ግብር ሊጀምሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በሕብረተሰብ ጤና የሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሐ ግብር ሊጀምሩ ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 3/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ በሕብረተሰብ ጤና የሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሐ ግብር ሊጀምሩ መሆኑ ተገለጸ።
ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን አገር አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና ዶክትሬት መርሐ ግብር ትምህርት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ አካሄደዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ዩኒቨርሲቲዎቹ ለዶክትሬት ትምህርቱ ያዘጋጁት የስርዓተ ትምህርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የሕብረተሰብ ጤና አመራር፣ አስተዳደር፣ ኮሙዩኒኬሽንና የፈጠራ አስተሳሰብ ክህሎት በመርሐ ግብሩ ትምህርት ከሚሰጥባቸው ዘርፎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የትምህርት መርሐ ግብሩ በሕብረተሰብ ጤና ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችና አመራሮችን በማፍራት የጤና ስርዓቱን ማሻሻልን አላማ ማድረጉ ተመላክቷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በሕብረተሰብ ጤና የሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሐ ግብር በ 2017 ዓ.ም እንደሚጀምሩና ተማሪዎችን እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል።
ለመርሃ ግብሩ እውን መሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተባብረው እንዲሰሩ የጤና ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴርና የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ የክልል ጤና ቢሮዎችና የጤና ተቋማት ተገኝተዋል።