የማልታ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የማልታ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 3/2016(ኢዜአ)፦ የማልታ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮ-ማልታ የመጀመሪያው ቢዝነስ ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የቢዝነስ ፎረሙ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና ማልታ ትሬድ በጋራ ያዘጋጁት ነው።
በፎረሙ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ በኢትዮጵያ የማልታ አምባሳደር ሮናልድ ሚካሌፍ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃና አርዓያሥላሴ፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የማልታ ትሬድ ኃላፊዎች እና ሌሎችም ተሳትፈዋል።
በዚሁ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ መንግስት የውጪ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረጉንና ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል።
በተፈጠረው ምቹ ሁኔታም የማልታ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሁለቱ አገራት ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ይበልጠ እንዲጠናከር ኢትዮጵያ ቁርጠኛ ናት ሲሉም አምባሳደሩ አክለዋል።
በኢትዮጵያ የማልታ አምባሳደር ሮናልድ ሚካሌፍ በበኩላቸው ማልታ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በንግድና በኢንቨስትመንት ይበልጥ አጠናክራ ትቀጥላለችም ብለዋል።
በማሪታይም፣በሳይበር ሴኩሪቲና በሌሎች ዘርፎች በጋራ እየተሰራ መሆኑን አምባሳደሩ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀና አርዓያሥላሴ በበኩላቸው ፎረሙ ኢትዮጵያ ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝም ገልጸዋል።
የማልታ ባለሃብቶችም በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በፋርማሲቲካል፣ በጤና ዘርፎች፣ በትምህርትና በሌሎች መስኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጅነር መላኩ እዘዘው በበኩላቸው ፎረሙ በኢትዮጵያና በማልታ መካከል ያለውን ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ በንግዱ ማህበረሰብ መካከል የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ፎረሙ በሁለቱ አገራት የንግድ ማህበረሰብ መካከል ወሳኝ ግንኙነት እንዲኖር መሰረት የሚጥል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የማልታ ትሬድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አንቶን ቡቲጂንግ ናቸው።