ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሲሸልስ የሚያደርገው በረራ ሀገሪቱን ከአፍሪካ ብሎም ከዓለም ጋር በማገናኘት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2016 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሲሸልስ የሚያደርገው በረራ ሀገሪቱን ከአፍሪካ ብሎም ከዓለም ጋር በማገናኘት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ በሲሸልስ የኢትዮጵያ አምባሳደር  እፀገነት በዛብህ ገለጹ። 

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እፀገነት በዛብህ ለሲሸልስ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዋቨል ራምካለዋን የሹመት ደብዳቤያቸውን አቅርበዋል፡፡ 

በሥነ-ስርዓቱ ወቅት የሲሸልስ ፕሬዝዳንት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ መሆንና ለዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ 


 

የሲሸልሱ ፕሬዝዳንት ሁለቱ ሀገራት በንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም መስክ ላይ አብሮ በመስራት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የሚረዳ ዕድል መኖሩን አንስተዋል። 

ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ፣ ክልላዊ እና አለማቀፋዊ መድረኮች ላይ ያላትን ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡ 

አምባሳደር እፀገነት በዛብህ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሲሸልስ የሚያደርገው በረራ ሀገሪቱን ከአፍሪካ ብሎም ከዓለም ጋር በማገናኘት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በመተሳሳይም አየር መንገዱ ካለው የካበተ የካርጎ አገልግሎት ሲሸልስ ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በንግድ ለማስተሳሰር ከፍተኛ ሚና የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም