ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዕጩ ዳኞችን ሹመት በሙሉ ድምፅ አጸደቀ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2016(ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ16ኛ መደበኛ ስብሰባው የቀረቡለትን የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች ሹመት መርምሮ አጽድቋል፡፡

የመንግስት ዋና ተጠሪ  ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የፍትህ ስርዓቱን ቀልጣፋ ለማድረግ እንዲሁም የተጀመረውን ሪፎርም ለማሳካት የዳኞቹ ሹመት ማስፈለጉን ገልጸዋል።

እጩ ዳኞች በፌደራል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ግልጽ በሆነ ማስታወቂያ መመልመላቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት የፅሑፍና የቃል ፈተና ከወሰዱ አመልካቾች መካከል ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ በእጩነት መመረጣቸውን አብራርተዋል።

የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ፤ ሥነ ምግባርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩባቸው ክልሎች ድረስ በመሄድና ሰፊ ማጣራት በማድረግ 16 እጩ ዳኞች መመረጣቸውንም አክለው ገልጸዋል።


 

የምልመላ ሂደቱ ግልፅ በሆነ መንገድ የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀው ለዕውቀትና ለብቃት ቅድሚያ በመስጠት የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ዳኞች ተመርጠዋል ብለዋል።

ምክር ቤቱ የቀረበለትን የዕጩዎች ዝርዝር በመመርመር በሙሉ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን የተሾሙ ዳኞች ቃለ መሀላ መፈጸማቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የኢትዮጵያ ሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት እንዲሁም የሕዝብ በዓላትንና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሠራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብንም መርምሮ አፅድቋል።     

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም