አዲሱ ትርክት ብዝኃነትንና አብሮነትን መሠረት ያደረገ ሊሆን ይገባል - የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ ትርክት ብዝኃነትንና አብሮነትን መሠረት ያደረገ ሊሆን ይገባል - የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2016(ኢዜአ)፦ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የሀገረ መንግሥት ግንባታውን ለማጠናከር አዲሱ ትርክት ብዝኃነትንና አብሮነትን መሠረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም ተናገሩ።
የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም የተቋሙን የስድስት ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ዘላቂ ሰላምን በመገንባትና የፌደራል ሥርዓትን ከማጎልበት አኳያ አበረታች ሥራ መሠራቱን ገልፀዋል።
በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት የማጠናከርና ግጭትን በመከላከል በኩልም የቅድመ መከላከልና የፈጣን ምላሽ ሥራዎች መልካም አፈጻጸም የታየባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
መልሶ ማቋቋም በተመለከተ ባለፉት ስድስት ወራት ከተለያዩ አካባቢዎች በግጭትና በተፈጥሮ አደጋ የተፈናቀሉ 111 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ገልፀዋል።
ይሁንና በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ኋላቀር የፖለቲካ ባህል አሁንም እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ የፖለቲካ ባህሉ ከሥር መሠረቱ መቀየር እንዳለበት አንስተዋል።
ከዚህ አንጻር በኃይል ሥርዓትን ለመቀየር የመሞከር አዝማሚያዎች ዛሬም መቀጠላቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተቃኘው በዚሁ የመጠፋፋት መንገድ መሆኑን ገልጸው፤ እስካሁን ድረስም እየተንከባለለ የመጣ የፖለቲካ ባህል ሆኗልም ነው ያሉት።
ይህንንም ተከትሎ የኃሳብ መለያየት ለመጠፋፋት ምክንያት ሊሆን እንደማይገባ ተናግረዋል።
አገሪቱን ወደ ግጭት አዙሪት የሚከታት ሚዛናዊነት የጎደለው ትርክትም ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የውይይት ባህል ካልዳበረ የቱንም ያህል ግጭትን ማስቆም ቢቻል ነገ ላይ ግጭት እንደማይፈጠር ዋስትና እንደማይሆን አስረድተዋል።
በመሆኑም ውይይትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸው፤ ጎን ለጎንም ብዝኃነትንና አብሮነትን መሠረት ያደረገ ትርክት ማጎልበት ይገባል ብለዋል።
በተለይም ገዥ ትርክቱ ቀደም ሲል የነበሩ ትርክቶች ያስከተሉትን ጉዳት በአግባቡ የፈተሸና ያንን ሊያርም የሚችል መሆን እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት።
ምንም ዓይነት የኃሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ሁሉም በጋራ መቆም እንዳለበት ገልጸው፤ "ሲመች ኢትዮጵያ ሳይመች ደግሞ ኢትዮጵያ ለኔ ምኔ ናት" የሚል አመለካከት ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ሰላምን በማስፈን ያላቸውን ሚና በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበው፤ በተቃራኒው ችግሮች እንዲባባሱ የሚሰሩ ደግሞ ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።