ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ  የባህር በር የማግኘት አለምአቀፍ ህጋዊ መብቷ እውን ለማድረግ ምሁራን ኃላፊነታችን ልንወጣ ይገባል-የህግ ምሁራን

ድሬደዋ፤መጋቢት 3 / 2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ  የህልውና መሠረት የሆነውን የባህር በር የማግኘት አለም አቀፍ ህጋዊ መብት እውን ለማድረግ ምሁራን ከመቼውም ጊዜ በላይ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የህግ  ምሁራን ገለጹ።

ለዚህም  የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊና በሰጥቶ መቀበል መርህ መጎልበት  እንዳለበትም አመልክተዋል።

የባህር በር የዓመታት ጥያቄ  ፍሬ እንዲያፈራ በዓለም አቀፍና በየመስኩ የሚገኙ ምሁራን ታሪካዊ ኃላፊነታችንን ከመንግስት ጎን ቆመን መወጣት ይኖርብናል ሲሉ ምሁራኑ ገልጸዋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የዓለምአቀፍ ህግ መምህርና ተመራማሪ አለምሰገድ ደጀኔ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ  ህልውናዋ ከባህር በር ባለቤትነት ጋር የተቆራኘ ነው።

በውጭ ጫናና በአገር ውስጥ በነበረው ችግር የኢትዮጵያ ህጋዊ መብት የሆነውን የባህር በር ባለቤትነት እንድታጣ መደረጉ ምሁሩ ታሪካዊ ዳራውን በማውሳት ገልጸዋል።

አሁንም አገራችን የጀመረችውን ጠንካራ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ስራዎች በላቀ ደረጃ በማሳደግ  የባህር በር ባለቤት የመሆን ዕድል ማስፋት ይኖርብናል ብለዋል።

ከተጎራባች አገራት ጋር ያላትን የጋራ ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት ማሳደግም እንዲሁ።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1982 በጃማይካ የተፈረመው የዓለም የባህር ህግ ስምምነትም የባህር በር የሌላቸው አገራት ወደብ ካለበት ቦታ የመድረስና የመመለስ እንዲሁም በባህር ውስጥ የሚገኙ ሀብቶችን ጭምር መጠቀምን ይፈቀዳል። 

ከዚህ አኳያ ህጉ ኢትዮጵያ የባህር በሮችን የመጠቀም መብት እንዳላትና  አጠቃቀሙ ከአገራት ጋር ባላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች አማካኝነት መፈጸም እንደሚቻል ተጠቅሷል።

እንደ ምህሩ ገለፃ ፤ ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት የህልውና ጥያቄዋ በዓለምአቀፍ ህግ የተረጋገጠ ሙሉ መብት ነው።

በአሁኑ ወቅት የተጀመረውን ጥረት ስኬታማ ለማድረግ በመላው ዓለም የሚገኙ ዲፕሎማቶችና ምሁራን ታሪካዊ ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን ሲሉ ምሁሩ ተናግረዋል።

አሁን ባለንበት ተለዋዋጭ ዓለም አቀፍ ክስተት አኳያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ለህልውናችን መሠረታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው በማለት ገልጸዋል።


 

ዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት መምህር እሼቱ እንዳይላሉ በበኩላቸው፤ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብቷ ወደ ተግባር ለማሸጋገር የጀመረችውን የሰጥቶ መቀበልና በጋራ የማደግ  ጥረቶችና የዲፕሎማሲ ስራዎችን መደገፍና ማጠናከር ይገባል።

የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የመኖር ያለመኖር የህልውና ጉዳይ መሆኑ ጠቁመው፤ ይህን እውነት ሁሉም ዜጋ ተረድቶ በየተሰማራበት መስክ የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም