ቀጥታ፡

መንግስት የትኛውም አይነት ጥያቄ አለኝ ከሚል ኃይል ጋር ውይይት ለማድረግ ዝግጁ ነው - ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2016(ኢዜአ)፦መንግስት የትኛውም አይነት ጥያቄ አለኝ ከሚል ኃይል ጋር ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሰላም ተቋም ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ) ጋር በመተባበር በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ ዓላማ  ያደረገ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል። 

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፤ ለዘላቂ የሰላም ግንባታ ሂደት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊታከልበት ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶች የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ ገናና ታሪክ የሚያጠለሹና ገፅታዋን የሚያበላሹ እንዲሁም ዜጎችን የሚጎዱ መሆኑን ገልጸዋል። 

በመሆኑም መንግስት የትኛውም አይነት ጥያቄ አለኝ ከሚል ኃይል ጋር ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በአማራ፣ ኦሮሚያና ሌሎችም አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በሃሳብ የበላይነት መፍትሔ ለመስጠት በቁርጠኝነት እየሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የሃሳብ ልዩነቶችን በሰለጠነ የምክክር ባህል መፍትሔ በመስጠት ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ አበክሮ እየሰራ ይገኛልም ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያ የሰላም ተቋም ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፤ ሌሎችም ለዘላቂ ሰላምና ልማት የድርሻቸውን አንዲወጡ ጠይቀዋል።


 

የኢትዮጵያ የሰላም ተቋም የቦርድ ሊቀመንበር አምባሳደር ሙሉጌታ ኢተፋ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያውያን ቅድመ አያቶቻችን በአርበኝነትና ጀብዱ ነፃነቷን አስጠብቀው አስረክበውናል ብለዋል።

አሁን ላይ ደግሞ ሰላምና አንድነቷን በማስጠበቅ ልማትና እድገቷን ለማረጋገጥ መስራት የዚህ ትውልድ አደራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የመንግስትን ጥረት አድንቀው ሌሎችም ይህንኑ መልካም አርአያ ሊደግፉት ይገባል ብለዋል።

የኃይማኖት አባቶች፣ የሲቪል ማበራት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች መንግስትን በማገዝ ለሰላም አበክረው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በአማራ ክልል የተከሰቱ ግጭቶች እያስከተሉት ያለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት በተመለከተ በመድረኩ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር እየተደረገባቸው ይገኛል።

 በመድረኩ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ፣ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደጀኔ ልመንህ፣ በዩ.ኤስ.አይ.ዲ የዴሞክራሲና የአስተዳደር ቢሮ ዳይሬክተር ስቴፋኒ ጋርቬይ ጨምሮ የመንግስት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበራት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የንግድ ማኅበራት፣ የኃይማኖት ተቋማት እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። 

የኢትዮጵያ ሰላም ተቋም እ.አ.አ. በ1992 የተቋቋመ ነፃ፣ ገለልተኛና ለትርፍ ያልተቋቋመ ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ነው።

በኢትዮጵያ የሰላም ግንባታና ግጭት አፈታት ተግባራትን በጥናትና ምርምር እንዲሁም የተቋማትን የአቅም ማጎልበት ረገድ ባለፉት 30 ዓመታት እየሰራ ያለ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም