አለም ባንክ ባለፉት ሶስት አመታት ለጤናው ዘርፍ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ኢንቨስትመንት አድርጓል-ጤና ሚኒስቴር 

አዲስ አበባ ፣መጋቢት 3/2016 (ኢዜአ)፡- አለም ባንክ ባለፉት ሶስት አመታት ለጤናው ዘርፍ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ኢንቨስትመንት ማድረጉን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ከአለም ባንክ የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን እና ቡድናቸው ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ 

በውይይታቸውም አለም ባንክ በኢትዮጵያ እየተገበራቸው የሚገኙ ፕሮጀክቶች ያሉበትን ደረጃ፤ እንዲሁም አለም ባንክ ባለፉት ሶስት አመታት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ኢንቨስትመንት ለጤናው ዘርፍ እንዳደረገ ተገልጿል፡፡  

ኢንቨስትመንቱ በዋናነት የሰው ሃብት ልማት፣ የጤና አገልግሎቶች በወረዳ ደረጃ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ እና ለጤና ማሻሻያዎች ትግበራ ላይ መዋሉም ታውቋል፡፡


 

አለም ባንክ  በተጨማሪም በኢትዮጵያ ክትባት ማምረት እንዲጀመር ድጋፍ  ማድረጉም ተገልጿል፡፡ 

አለም ባንክ የኢትዮጵያን የጤና ስርዓትን ለማዘመን ዲጂታላይዜሽን ላይ ኢንቨስት በማድረግ ፣ ለወደሙ ተቋማት መልሶ ማቋቋም እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረጉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ 

አለም ባንክ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየተገበረ የሚገኘው የጤና ተቋማት እድሳት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም በውይይቱ መግባባት ላይ መደረሱን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

በመድረኩ ጤና ሚኒስቴር እና አለም ባንክ ወደፊት በትብብር ሊሰሩባቸው የሚችሉባቸው መስኮች ላይም መክረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም