ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል ጤናና ማህበረሰብ ተኮር ስርዓተ ምግብን ለማሻሻል የሚያስችሉ የአምስት ዓመት ፕሮጀክቶች ይፋ ተደረጉ

 መቐለ፤ መጋቢት 2/2016(ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል የጤና አገልግሎትን እና የማህበረተሰብ ተኮር ስርዓተ ምግብን ለማሻሻል በአምስት አመታት ውስጥ የሚተገበሩ ሶስት ፕሮጀክቶች ይፋ ተደረጉ።

በቀጣዮቹ አምስት አመታት ውስጥ ተግባራዊ ለሚደረጉት የማህበረሰብ ተኮር ስርዓተ ምግብ፣ የጤና ባህርይ እና የጤና ተቋማት ጥራት ማሳደግን አላማ ላደረጉት ፕሮጀክቶች 154 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በጀት መመደቡም ተገልጿል። 

ፕሮጀክቶቹ ከዚህ ቀደም ተግባራዊ ሲደረጉ የነበሩ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና አጋር አካላት በተገኙበት ይፋ ተደርገዋል። 

በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስቴር ተወካይና የሰቆጣ ቃል ኪዳን (ዲክላሬሽን) ፕሮግራም ማናጀር ዶክተር ሲሳይ ሲናሞ እንደገለፁት፤ ለጤና እና ለስርዓተ ምግብ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያገኙ መንግስት ከባለድርሻ አካላት በመተባበር እየሰራ ይገኛል። 

የጤና ችግር መንስኤ የሆኑ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ለመፍታት የጤና ሚኒስቴር ከሀገር ውስጥና ከአለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 


 

በትግራይ ክልል ተግባራዊ የሚደረጉት ፕሮጀክቶች ለጤና አገልግሎትና ለስርዓተ ምግብ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትና በክልሉ የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲኖር ትልቅ አቅምን ይፈጥራል ብለዋል። 

ፕሮጀክቶቹ በክልሉ በ44 ወረዳዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ የገለፁት ደግሞ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አማኑኤል ሃይለ ናቸው። 

የክልሉን የጤና አገልግሎት መልሶ በመገንባትና ሰርዓተ ምግብን በማሻሻል የትግራይን ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለዋል።

በዩ ኤስ ኤይድ ኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ሃላፊ ሚስተር ጆናታን ሮዝ በበኩላቸው ድርጅታቸው የኢትዮጵያ አጋር መሆኑን እና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የተለያዩ የጤና ዘርፎች ዙሪያ በ500 የአገሪቱ ወረዳዎች ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በትግራይ ክልል ተግባራዊ የሚደረጉ እነዚህ ፕሮጀክቶች በተለይ የእናቶችና ህፃናት ጤናን ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም ኃላፊው ተናግረዋል። 

ድርጅቱ ትግራይን ጨምሮ የሌሎች ክልሎች የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሳደግ ከመንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል። 

በአገር አቀፍ ደረጃ የማህበረሰብ ተኮር ስርዓተ ምግብ፣ የጤና ባህርይ እና የጤና ተቋማት ጥራትን ለማሳደግ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ተግባራዊ ለሚደረጉ ፕሮጀክቶች 154 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በጀት መመደቡን ለማወቅ ተችሏል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም