ቀጥታ፡

የኩላሊት ምርመራና ሕክምና አገልግሎት ለማስፋት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2016 (ኢዜአ)፦የኩላሊት ምርመራና ሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስቴር  አስታወቀ፡፡

ዓለም አቀፉ የኩላሊት ቀን ”የኩላሊት ጤና ለሁሉም፤ ላልታሰበው መዘጋጀት፤ ለተጋለጡት ድጋፍ” በሚል መሪ ቃል  በዓለም ለ18ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ 17ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች ተከብሯል።

እ.ኤ.አ በ2019 የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት የኩላሊት ሕመም ከ100ሺህ ሰዎች ውስጥ 24 ሰዎችን ለሞት በመዳረግ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ውስጥ በ6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

በኢትዮጵያም  ለኩላሊት ሕመም ከሚዳርጉ ዋነኛ መንስዔዎች መካከል ከፍተኛ የደም ግፊትና የስኳር ሕመም ይገኙበታል፡፡

በጤና ሚኒስቴር  የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ዘርፍ ተላላፊ ያልሆኑ በሸታዎችና የአዕምሮ ጤና ዴስክ ኃላፊ ዶክተር ሰላማዊት አየለ  እንዳሉት፤ ሥር የሰደደ የኩላሊት ሕመም በኢትዮጵያ ዋነኛ  ከሆኑ የኅብረተሰብ ጤና ችግሮች መካከል አንዱ ነው።

በሽታው በግለሰብም ሆነ በሀገር ላይ እያደረሰ የሚገኘውን ተፅዕኖ ለመከላከል የጤና ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኩላሊት ሕመምን አስቀድሞ ለመከላከል  ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን መከተል፣  የጨው መጠን መቀነስ፣ ሲጋራ ያለማጨስ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘወተር፣ ከአልኮል መጠጦች በመቆጠብና የሰውነት ክብደትን በማስተካከል አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር በሽታውን  ለመከላከል  የኩላሊት ሕመምን ያካተተ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ለደም ግፊትና ስኳር ሕመም ቅድመ ምርመራ ማድረግ፣ መመርመርና ማከም፣  መቆጣጠርና ሥር የሰደደ የኩላሊት ሕመምን መከላከል  ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው ብለዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ኩላሊት ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ልሳን  ሰይፉ በበኩላቸው፤ የኩላሊት ሕመም በዓለም ላይ ስጋት እየሆኑ ከመጡ ሕመምች አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ሕብረተሰቡ በየጊዜው የጤና ምርመራዎችን በማድረግ የራሱን  እና ቤተሰቡን ጤና መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የቀኑ መከበር ዋነኛ ዓላማም ለሕሙማኑ እና ለምርመራ ለሚመጡ የኅብረተሰብ  ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን መስጠት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በበዓሉ አከባበር  ላይ የተገኙት የኅብረተሰብ ክፍሎችም ነፃ የደም ግፊት፣ የስኳር እና የኩላሊት ምርመራ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም