አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከተለያዩ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከተለያዩ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2016(ኢዜአ) ፦ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከተለያዩ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
አምባሳደር ስለሺ ከካሊፎርኒያ የምክር ቤት ተወካይ ቴድ ሊዩን ጋር ባደረጉት ውይይት በተለይ በኢትዮጵያ ስላለው የሰላም ሂደትና በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ስለሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከአጎዋ መውጣቷና ያስከተለውን ተጽእኖ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አምባሳደሩ በአሜሪካ ዲፓርትመንት የኢኮኖሚና ቢዝነስ ጉዳዮች ቢሮ የበጎ ፈቃደኞች እና የፋይናንስ ጉዳዮች ተጠባባቂ ምክትል ረዳት ፀኃፊ ከተመራ ልኡክ ጋርም የዋጋ ንረትን በሚያባብሱ የጥቁር ገበያ እና ሀገሪቱ እያጋጠሟት ስለሚገኙ የፋይናንስ ዘርፉ ችግሮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ ረዳት የንግድ ተወካይ ኮንስታንስ ሃሚልተን ጋር የተገናኙት አምባሳደሩ ፥ ኢትዮጵያን ወደ አጎዋ መመለስ ስለሚቻልበት ሁኔታ መወያየታቸውን አምባሳደሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ከአጎዋ መነጠል በተለይ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ሴቶችና ወጣቶች የስራና ኑሮ ሁኔታ ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ያብራሩት አምባሳደር ስለሺ ውሳኔው በአሜሪካ ባለሃብቶች ላይ ተጽኖ እንደሚያሳድርና በግጭት እና በአደጋ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ላይ ጫና እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
አምባሳደሩ በአሜሪካ የአልጄሪያ አምባሳደር ሳብሪ ባኦንካደም ጋርም በሁለቱ ሀገራት መካከል ስላለው የሁለትዮሽ ግንኙነት መምከራቸውን አምባሳደሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።።
አምባሳደር ስለሺ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እንዲሁም ከተባበሩት መንግሰታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ዩኤን ዲፒ ተወካይ ባሲል ማሴ ጋር የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አሁናዊ ሁኔታን በተመለከተና የኮሚሽኑን ሀብት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ተወያይተዋል።