ቀጥታ፡

ባለፉት ሰባት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የእንስሳት ክትባት 665 ሺህ ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2016(ኢዜአ)፦ የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ባለፉት ሰባት ወራት ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለገበያ ካቀረበው የእንስሳት ክትባት 665 ሺህ ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገለፀ። 

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ታከለ አባይነህ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ አሁን ላይ 23 ዓይነት የእንስሳት ክትባት እያመረተ ይገኛል።

ክትባቶቹንም ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንዲሁም ቀሪውን ደግሞ ወደ ተለያዩ የምዕራብና የማዕከላዊ አፍሪካ አገራት እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ሰባት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበው 175 ሚሊየን ዶዝ ክትባት 665 ሺህ ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልፀዋል።

ኢንስቲትዩቱ ክትባቱን ለምስራቅ አፍሪካ አገራት በማስተዋወቅ የገበያ ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአገር ውስጥም ወደ ተለያዩ ክልሎች ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የግል ባለኃብቱ በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የእንስሳት መድኃኒቶች የምዝገባና ፈቃድ ሥራ እየሰራ መሆኑን አንስተው፤ ምርቶች የማስተዋወቅ ሥራ አብሮ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የእንስሳት መድኃኒቶችን ወደ ገበያ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን በመግለፅ።

ኢንስቲትዩቱ በዓመት ወደ 350 ሚሊየን ዶዝ ክትባት እያመረተ ቢሆንም የምርት መጠኑ የአገር ውስጥንና የውጭ ተጠቃሚዎችን የክትባት ፍላጎት የሚያሟላ አይደለም ብለዋል። 

በመሆኑም ይህንን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም