ቀጥታ፡

ኦቪድ ግሩፕ ለኢትዮጵያ ሪል ስቴት ዘርፍ ትምህርት የሚሰጥ አርዓያ ድርጅት ነው - የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ቦርድ ሊቀ-መንበር ግርማ ሠይፉ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2016(ኢዜአ)፦ ኦቪድ ግሩፕ ለኢትዮጵያ ሪል ስቴት ዘርፍ ትምህርት የሚሰጥ አርዓያ ድርጅት መሆኑን የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ቦርድ ሊቀ-መንበር ግርማ ሠይፉ ገለጹ።

የኦቪድ ግሩፕ እህት ኩባንያ የሆነው ኦቪድ ሪል ስቴት ይፋዊ የማስጀመሪያና ለአንድ ቀን የቆየ የታላቅ ቅናሽ የቤት ሽያጭ መርሃ-ግብር ማጠቃለያ መድረክ ትላንት ተካሂዷል። 

የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ቦርድ ሊቀ-መንበር የሆኑት የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ግርማ ሠይፉ በዚሁ ጊዜ፤ ኦቪድ ለግንባታው ዘርፉ አርዓያ የሆነ ድርጅት ነው ብለዋል። 

ኦቪድ በ90 ቀናት ባለ11 ወለል አፓርታማ ገንብቶ ማስረከቡን አስታውሰው፤ በአጭር ጊዜ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች በማስረከብ የቤት ገበያ ዋጋ እያረጋጋ መምጣቱንም ተናግረዋል።   

ይህም ኦቪድ በዘርፉ ካስተዋወቃቸው የሥራ ባህሎች መካከል በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸው፤  ሌሎች በዘርፉ ያሉ ኩባንያዎችም የቤት ፍላጎትን ተደራሽ ለማድረግ መሥራት አለባቸው ነው ያሉት።

በተለይም ትንሽ ሰርቶ ብዙ ማትረፍ በተለመደበት የሪል ስቴት ገበያ ኦቪድ ትርፍን ከብዛት የማግኘት ስልቱም በበጎ የሚወሰድና እንደ ኩባንያ ለየት የሚያደርገው መገለጫው እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የንግድ ኩባንያዎች ከፉክክር ይልቅ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባቸው ገልፀው፤ በዚህ ረገድ ኦቪድ ከሌሎች የውጭ ኩባንያዎች ጋር በአጋርነት ለመሥራት ያለውን ተሞክሮ አድንቀዋል። 

የኦቪድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሠ በበኩላቸው፤ የኦቪድ ግሩፕ እህት ኩባንያዎች ራዕይ ኢትዮጵያን ማልማት ነው ብለዋል።


 

ኦቪድ ሪል ስቴት 64 ሺህ ቤቶች እያለማ መሆኑን ገልፀው፤ ከእነዚህ መካከል 90 በመቶዎቹ በመንግሥትና ግል አጋርነት የሚለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በቅርቡ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የ5 ሺህ ቤቶችን ሽያጭ ለማድረግ ከኦቪድ ጋር ሥምምነት መፈፀሙን የድርጅቱን የመፈጸም ደረጃ እንደሚያሳይ ገልፀዋል።  

ትውልደ-ኢትዮጵያውያንን ለማሳተፍ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በአጋርነት እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ኩባንያው ማኅበራዊ ኃላፊነቱንም በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህንም ተከትሎ እስካሁን 500 መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ በነፃ መለገሱን፣ ከ2 ሺህ በላይ እናቶችን ተጠቃሚ ያደረገ የእንጀራ ፋብሪካ ገንብቶ ማስረከቡንና በሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶችም የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም ኦቪድ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው፤ በቤቶች ልማት ያለውን ተሳትፎ በማሳደግ በዘርፉ አዎንታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

ትናንት በተካሄደው የኦቪድ ራዕይ 2024 ኤክስፖ የቤት ሽያጭ መርሃ-ግብር 1 ሺህ 500 ሰዎች የ40 በመቶ ቅናሹን ዕድል በመጠቀም ለግዥ መመዝገባቸውን ገልፀዋል። 

በመርሃ-ግብሩ የጫካ መኖሪያ ቤት፣ ሐረር ሆራይዘን፣ ኪንግስ ታወርና አፍሪካን ኃይትስ የተሰኙ በላቀ ጥራት የሚገነቡ አራት የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶችን ማስተዋወቅ ተችሏል ተብሏል። 

በመርሃ-ግብሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ፣ የዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የዘርፉ ኩባንያ ተወካዮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም