አንጋፋው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኛ እዮብ ግደይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ - ኢዜአ አማርኛ
አንጋፋው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኛ እዮብ ግደይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 1/2016(ኢዜአ)፦ አንጋፋው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የዓልዓለም ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እዮብ ግደይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ጋዜጠኛ እዮብ ግደይ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስር በአረብኛ ቋንቋ በምትታተመው ዓልዓለም ጋዜጣ ለረጅም አመታት በተለያዩ የሥራ መደቦች በታታሪነትና በትጋት አገልግሏል።
ጋዜጠኛ እዮብ ግደይ ህይወቱ እስካለፈበት እለት ድረስም የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሠርቷል።
እዮብ በተለይም ለሙያው ያለው ፍቅርና ክብር ላቅ ያለ በመሆኑ የአገሩን ጥቅምና ክብር የሚያስጠብቁ ልዩ ልዩ ጽሁፎችን በአረቡ ዓለም ጋዜጦች እና ድረገጾች ሳይቀር ማሳተም የቻለ አንጋፋ ጋዜጠኛ ነበር።
ጋዜጠኛ እዮብ ግደይ ዛሬ ረፋድ ላይ በድንገት ህይወቱ ማለፉን ኢፕድ ከቤተሰቦቹ ማወቅ ችሏል።
ጋዜጠኛ እዮብ ግደይ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለቤተሰቦች ወዳጅ ዘመዶችና የሥራ ባልደረቦቹ መጽናናትን ይመኛል።