መገናኛ ብዙሃን ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል
አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 1/2016(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ።
ከተለያዩ የግል መገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለአራት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።
በማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ ተገኝተዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤መገናኛ ብዙሃን የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅና ሥርዓት ግንባታ ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በማስቀደም አገራዊ መግባባት ላይ በሚጠበቀው ደረጃ እየሰሩ እንዳልሆነ ገልጸው ሕዝቡን የሚያቀራርቡ እንድነትን የሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ዘንድ ሚዛናዊ ሆኖ ከመዘገብ ይልቅ ወገኝተኝነት እየተስተዋለ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ይህም ለሰላም እና አገር ግንባታ ሳንካ በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
መገናኛ ብዙሃን በስራዎቻቸው አገርን ማስቀደም እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
በመድረኩ የውይይት መነሻ ያቀረቡት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን አብሮ የሚያኖር ነገር እየሰራን ነው ወይ?፣ትውልድ እየገነባን ነው የሚለውን ቆም ብለው ሊያጤኑት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አቅም ማነስ፣የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ እንዲሁም የግንዛቤ ክፍተቶች በአግባቡ እንዳይሰሩ ከሚያደርጉዋቸው ምክንያቶች መካከል ይገኙበታል።
በቀጣይም መገናኛ ብዙሃን የሕግና ሙያዊ ሥነ ምግባር ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ስልጠናዎች መስጠት እንዲሁም ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ መተግበር ላይ መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የአዋሽ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጋዜጠኛ አህመድ አደም የግል መገናኛ ብዙሃን ገቢ በሚያስገኙ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ማድረጋቸው በብሔራዊ ጥቅምና አገራዊ መግባባት ዙሪያ ትኩረት አድርገው እንዳይሰሩ ማድረጉን ነው የተናገረው፡፡
መገናኛ ብዙሃን በተለይ ማህበረሰብን ማስተማርና ማንቃት ላይ ትኩረት ማድረግ አንዳለባቸውም ነው የተናገረው፡፡
ከአራዳ ኤፍ ሬዲዮ ጣቢያ የመጣው ጋዜጠኛ ዳዊት በሪሁን በበኩሉ በአንዳንድ መረጃ ሰጪዎች ዘንድ የሚስተዋለው መረጃ ያለመስጠት ችግር መገናኛ ብዙሃን በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሰሩ እክል መፍጠሩን ነው ያነሳው፡፡
ማህበራዊ ሚዲያው እየፈጠረ ያለው አሉታዊ ጫናም ቸል ሊባል እንደማይገባው የተናገረው ደግሞ የአዲስ ዋልታ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሳሙኤል ዳኛቸው ነው።
በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ መረጃዎችን በተገቢው መልኩ ማጥራት እንደሚገባም እንዲሁ፡፡